መምሪያው ለመጀመሪያ ዙር የሚሰጠውን የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ በዳውሮ ዞን ዋካ ከተማ ከዞኑ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የጤና ባለሙያዎች ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
ስልጠናው የተሰጠው “ሕፃናትን በማስከተብ ፖሊዮ ሊያስከትል ከሚችለው የአካል ጉዳትና ሞት እንጠብቃቸው” በሚል መሪ ቃል ነው።
የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ተስፋዬ ከተማ በሥልጠና ወቅት እንደገለጹት፤ ሰልጣኞች ያገኙትን ግንዛቤ ተጠቅመው ቀጣይ በወረዳና ከተማ አስተዳደር ደረጃ በሚሰጠው ስልጠና ለሰልጣኞች ተገቢወን ግንዛቤ በመፍጠርና ጠንከር ያለ የክትትል ስርዓት በመዘርጋት ውጤታማ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
አቶ ተሰፋዬ አክለውም፤ ከፖሊዮ ክትባቱ ጎን ለጎንም መደበኛ ክትባት ጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ያቋረጡ ህጻናትን የመለየትና ክትባት እንዲያገኙ የማድረግ እንዲሁም ፖሊዮ መሰል በሽታ ቅኝት እና አስሳ፣ ኢቦላ ቫይረስ ቅኝት እና አሰሳ በመደበኛ ክትባት ተደራሽ ያልሆኑ ወይም ጀምረው ያቋረጡ ህፃናትን የመለየት እና የመከተብ አገልግሎት እንዲሁም የእናቶች እና ህፃናት የምግብ እጥረት ልየታ ከዘመቻው ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰጥም ጨምረው ገልጸዋል።
የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እንደ ሀገርም ለመጀመሪያ ዙር ከህዳር 11 እስከ ህዳር 14 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ በዞኑ ጤና መመምሪያ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት እና ምላሽ ቡድን አስተባባሪ አቶ ወልደ በካሎ ገልጸዋል።
አቶ ወልደ በዞኑ ለ1 መቶ 28 ሺ 8 መቶ 74 ህፃናት ክትባት እንደምሰጥ ገልፀው፤ የፖሊዮ በሽታ ለመከላከል ከ5 ዓመት በታች ያሉትን ህፃናት ቀደም ሲል ክትባት የወሰዱና ያልወሰዱ ጭምር በክትባቱ እንደምሳተፉ አስታውቀዋል።
የስልጠናው ዋና ዓላማም ባለሙያዎችን በማብቃት በሽታው የሚያደርሰውን ሞትና የአካል ጉዳት መከላከል መሆኑን ጠቁመው፣ የፖሊዮ ቫይረስን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ ላለው ዘርፈ ብዙ ስራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዘመቻውን በስኬት ለማጠናቀቅ ስልጠናው ከፍተኛ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸው፣ ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የአሰልጣኞች ሥልጠና በኢትዮጵያ (AFENET) የAfrica Field Epidemiology Network ባለሙያ እና የዳውሮ ዞን አማካሪ አይዛክ፣ አንድም ህፃን የፖሊዮ ክትባት ሳይከተብ እንዳይታለፍ ክትትል እና ድጋፍ ሥራ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በአሰልጣኞች ሥልጠና የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ማኔጅመንት አካላትን ጨምሮ ከሁሉም ከወረዳና ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤቶች የተውጣጡ ጤና ባለሙያዎች የሥርዓተ ምግብ፣ የድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት እና የህክምና ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት አስተባባሪዎች በሥልጠናው ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ: አንዱዓለም ኡማ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሙሉ ወጪ የተገነባው የዱዛ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ህንፃ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሐይማኖቱ መሪዎችና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመረቀ
ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በቤተሰብ እና በጎሳ ደረጀ የሚያደርጉት ባህላዊ የምርቃት ስርአት በየአካባቢው እና በሀገር ደረጀ አንድነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን በማስፈን የመንግስትን የሰላም ግንባታ ግብ ከስኬት ለማድረስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የሀዲያ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ገለጸ።
የቪክቶር ዮኬሬሽ አስደናቂ የብሔራዊ ቡድን ግስጋሴ ቀጥሏል