በግብርናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ወደ ተግባር መገባቱ ተገለፀ

በግብርናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ወደ ተግባር መገባቱ ተገለፀ

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በግብርናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ወደ ተግባር መግባቱን በጌዴኦ ዞን የራጴ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገለፀ።
‎
‎የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በላይ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጎልበት ጠንክረው እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
‎
‎የራጴ ወረዳ  ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ  አቶ ደንበኙ ደምሴ፣ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሕብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‎
‎ቀደም ሲል በወረዳው በግብርናው የልማት ዘርፎች የነበሩ ጠንካራ ውጤቶችን በይበልጥ ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለማረም አብይ ኮሚቴ ተዋቅሮ በቀጣይ ተግባሩን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
‎
‎አቶ ደንበኙ አያይዘውም፣ ያለውን የሰው ኃይልና ዕምቅ አቅም በመጠቀም በግብርና ዘርፍ እመርታ ለማስመዝገብ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
‎
‎‌በቀጣይ በ2ኛ ሩብ ዓመት  ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራ በትኩረት እንዲሰራም አጽንኦት ይሰጥበታል ብለዋል።
‎
‎በተለይም ገብስ፣ ስንዴ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ሽንኩርት፣ ጎመን ምርቶችና መሰል የልማት መስኮች በ2019 የምርት ዘመን በልዩ ትኩረት የሚሰራባቸው በመሆኑ ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየተሰጡ እንደሚገኝም ኃላፊው አስታውቀዋል።
‎
‎በከብቶችና በዶሮ እርባታ፣ በበግ ማሞከት፣ በንብ ማነብና የተራራ ላይ የማር ልማት ዘርፍ በወረዳው የተጀመሩ አበረታች ሥራዎችን ለማስፋፋት በሕብረተሰቡ ዘንድ በንቅናቄ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
‎
‎አርሶ አደር በየነ አስራት እና መኩሪያ በራሶ በወረዳው የድሬቶና የወካዲቢቱ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም በላይ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጎልበት ጠንክረው እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
‎
‎ለምግብነት ከሚውሉ ሰብሎች በተጨማሪ የቡና ልማትን በማስፋፋት ለዕድገት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት ጥራት ያለውን የቡና ዘር እያዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዚህም የግብርና ባለሙያዎች እገዛ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል።
‎
‎በመጨረሻም ዘላቂ የኑሮ መሠረት በመፍጠር ከጥገኝነትና ከተረጂነት ለመላቀቅና በራስ አቅም ለመቆም የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት በልዩ ትኩረት  እየሠሩ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል።
‎
‎ዘጋቢ:- እስራኤል ብርሃኑ- ከይርጋጨፌ ጣቢያችን