የምርት አሰባሰብ ዘመቻው በተቀናጀ መንገድ እንዲካሄድ ጥሪ ቀረበ

የምርት አሰባሰብ ዘመቻው በተቀናጀ መንገድ እንዲካሄድ ጥሪ ቀረበ

የደረሱ የሰብል ምርቶች ለብክነት እንዳይዳረጉ የምርት አሰባሰብ ዘመቻው በተቀናጀ መንገድ እንዲካሄድ የስልጤ ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ።

የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙበራ ከማል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት በማሳ ላይ የደረሱ የሰብል ምርቶች ለብክነት እንዳይዳረጉ፣ በሚካሄደው የምርት አሰባሰብ ዘመቻ ሁሉም የዞኑ መዋቅሮችና ማህበረሰቡ በተቀናጀ መንገድ መረባረብ አለባቸው ሲሉ ጥሪ ቀርበዋል።

በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ፣ የደረሱ ሰብሎች እንዳይበላሹና ለብክነት እንዳይጋለጡ የምርት አሰባሰብ ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል።

ኃላፊው እንደገለጹት በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ105 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

በተጨማሪም ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ የለማ በመሆኑ፣ የደረሱ ሰብሎችን በአጭር ጊዜ ለመሰብሰብ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኮምባይነር መሰብሰብ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፤  አነስተኛ ማሳዎችን ደግሞ የቤተሰብ ጉልበት በማሰባሰብ ምርቱን በአፋጣኝ መሰብሰብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የአየር ንብረት ሳቢያ በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች የምርት መቀነስ መከሰቱን የተናገሩት አቶ ሙበራ፤ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ በከፍተኛ ጥረት የተመረተው የግብርና ምርት በአጨዳ፣ በክምር፣ በመጓጓዣና በአውድማ ወቅት ለብክነት እንዳይዳረግ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ይህንን ለማካካስም የጸደይ እርሻና የመስኖ ልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን፣ የተፈጠረውን የአፈር እርጥበት ለሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች በአግባቡ በመጠቀም የምርት ጉዳትን ለማካካስ በተለየ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የምርት ብክነትን መከላከል የአርሶ አደሩ ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የመላው ማህበረሰብና የባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም የዞኑ መዋቅሮች፣ ባለሙያዎችና ማህበረሰቡ በደቦና በተቀናጀ ጥረት የደረሰውን ምርት ከብክነት በመታደግ የዘንድሮውን የምርት ግብ ለማሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዞኑ በኩታ ገጠም እርሻ የለሙ ሰብሎችን በኮምባይነር በመጠቀም በፍጥነት የመሰብሰብ ሥራ ከመሊቅ የስልጤ አርሶ አደሮች ህብረት ስራ ዩኒየን ጋር በመተባበር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “እኔ እያለሁ አንድም ፍሬ ምርት አይባክንም” በሚል መርህ የደረሱ የሰብል ምርቶች ለብክነት እንዳይዳረጉ የምርት አሰባሰብ ዘመቻው በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ ይገኛል።

ዘጋቢ፦ ሙጂብ ጁሀር- ከሆሳዕና ጣቢያችን