‎የይርጋጨፌ ቡናን ጥራቱን አስጠብቆ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ተጠቆመ

የይርጋጨፌ ቡናን ጥራቱን አስጠብቆ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ተጠቆመ

በልዩ ተፈጥሯዊ ጣዕሙ በዓለም የሚታወቀውን የይርጋጨፌ ቡና ጥራቱን አስጠብቆ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የወረዳው ቡናና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ጽ/ቤት አስታወቀ።

‎

‎በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ አምራች አርሶ አደሮች በበኩላቸው የቡናን ጥራት አስጠብቀው ለገበያ ለማቅረብ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎

‎የይርጋጨፌ ወረዳ ቡናና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ አሰፋ እንደተናገሩት፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቡናን ጥራት ለማስጠበቅና ሕገወጥ ዝውውርን ለመከላከል ግብረ ሃይል በማቋቋም እየተሰራ ይገኛል።

‎

‎‌በ2019 የምርት ዘመን 46 ሺህ 686 ቶን ቡና ለመሰብሰብና 26 ሺህ 500 ነጥብ 22 ቶን የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለመላክ ታቅዶ እስካሁን 57 በመቶ ተግባራዊ መደረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል።

‎

‎አያይዘውም ከአንድ ሄክታር መሬት የሚገኘውን አማካይ የቡና ምርት ለማሳደግ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በቡና ምርት ጥራትና ብዛት ላይ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የሞዴል አርሶ አደሮችን ቁጥር ለማሳደግም ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

‎

‎የተሻለ የቡና ዝርያ አጠቃቀምን ማስፋፋት፣ የእርሻ መሬትን በተገቢው መንከባከብና የአርሶ አደሮችን የምርት አያያዝ ክህሎት ማጎልበት ለቡናው ጥራትና ምርታማነት መጨመር አስፈላጊ ነው ሲሉ አቶ አበራ አክለዋል።

‎

‎በተለይም የቡና ፍሬን በትክክለኛው የብስለት ደረጃ መልቀምና በንጽሕና መያዝ የምርቱን የገበያ ተፈላጊነትን ከማሳደግ ባለፈ የአምራቾችን ገቢ ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሰፋፊ የቡና ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራም በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቁመዋል።

‎

‎አርሶ አደር ጌታነህ ግርማ እና አስራት ደያሶ በወረዳው የኤላጠኔቻ እና ቆንጋ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው። ቡናን ከዘር መረጣና ችግኝ ተከላ እስከ ፍሬ መሰብሰብ ድረስ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ በጥራትና በብዛት እያመረቱ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

‎

‎ለምርት የደረሰና የቀላ ቡና ብቻ በመልቀምና በንጽሕና በመያዝ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ እያቀረቡ በመሆናቸው፣ ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

‎

‎መንግሥት በቡና ዋጋ ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ መዋዠቅ በመቅረፍ፣ አልፎ አልፎ በግብይት ዙሪያ የሚታዩ ሕገ ወጥ አሠራሮችን ማስተካከል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

‎

‎ዘጋቢ:- እስራኤል ብርሃኑ- ከይርጋጨፌ ጣቢያችን