ግብር የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ፣ የልማት ዋልታና የዜጎች የጋራ ቃልኪዳን ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ
ግብር የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ፣ የልማት ዋልታና የዜጎች የጋራ ቃልኪዳን መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ለኢኮኖሚው መነቃቃት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑም ተጠቁሟል።
ቢሮው ክልል አቀፍ የዕለት ግብር ግመታ ዙሪያ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከዞን፣ ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች፣ ወረዳና ከከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ባለሙያዎች፣ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ደግፌ፤ ግብር የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ፣ የልማት ዋልታና የዜጎች የጋራ ቃልኪዳን መሆኑን አውስተው የምንገነባቸው ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት መንገዶችና የመሰረተ ልማት አውታሮች እውን የሚሆኑት እያንዳንዱ ዜጋና ነጋዴ ግብርን በታማኝነት ሲከፍል መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በንግዱ ዘርፍ ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ለኢኮኖሚው መነቃቃት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድማገኝ፤ የገቢ ግመታ ዋና አላማው ግብር ከፋዩን መጉዳት ሳይሆን ፍትሃዊ፣ ግልፅና ተዓማንነት ያለው የግብር አከፋፈል ስርዓት መዘርጋት ነው ብለዋል።
የገማች ኮሚቴ አባላትና ባለሙያዎችም ስራው የመንግስትን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ዜጎች በመንግሥት እና በታክስ ስርዓቱ ላይ ያላቸውን እምነት የሚገነባ በመሆኑ በከፍተኛ ኃላፊነት፣ ታማኝነትና ሙያዊ ሥነምግባርን በመጠበቅ እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የግመታ ቡድኖች ወደ ንግድ ግመታ ሲመጡ ትክክለኛውን የዕለት ሽያጭና የንግድ እንቅስቃሴ መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብር እንዲያደርጉ ለንግዱ ማህበረሰብ ጥሪ ያስተላለፉት የቢሮው ኃላፊ፤ ይህም ፍትሃዊ ግብር እንዲወሰን ከማድረጉም ባሻገር በገበያው ውስጥ ጤናማ ውድድር እንዲሰፍን ያደርጋል ሲሉ አሳስበዋል።
በክልል አቀፍ የዕለት ግብር ግመታ ስልጠናው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ደግፌ፤ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የታክስ ስርዓት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ልሳነወርቅ ካሳዬ፣ የክልሉ ንግድና ማህበራት ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ቢታኔን ጨምሮ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከዞን፣ ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች፣ ወረዳና ከከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ባለሙያዎች፣ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
ታሪካዊና ጥንታዊው – ምሁር ኢየሱስ ገዳም
የቱሪዝም ዘርፍ በመደመር መንግስት የብልፅግና ተምሳሌት እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው