የመሬት ኩታ ገጠም የአስተራረስ ስርአትን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገለፁ
በመሬት አጠቃቀም መመሪያና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፤ እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ ለማፋጠን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ብልፅግናን በማህበረሰብ ደረጃ እውን ለማድረግና የምግብ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ዋነኛ መሰረት የሆነውን የመሬት ሀብት በተቀናጀ መልኩ መጠቀም አይነተኛ ሚና እንዳለው አቶ ኡስማን አስረድተዋል።
የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋነኛ መሰረት የሆነው ግብርናን በማዘመንና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግበር በዘርፉ የሚጠበቀውን ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ምርታማነት ስንል መሬትን ብቻ አይደለም የሚሉት የቢሮ ሀላፊው የአምራች ጊዜና ጉልበት የማምረቻ መሳሪዎችን ጭምር ያጠቃለለ ነው ብለዋል።
በዚህም እንደ ክልል ከተናጠል ይልቅ ያሉ አቅሞችን በማስተባበር ከ2 ሺህ እስከ 35 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ኩታ ገጠም ሜጋ ክላስተር መፍጠር መቻሉንም አቶ ኡስማን አስረድተዋል።
ሜጋ ክላስተር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ላይም ተጨማሪ የሆነ የምርታማነት እድገት ማስመዝገብ ተችሏልም ብለዋል።
በአጠቃላይ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ከዘርፉ የሚጠበቀውን የምርታማነት ግብ ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የመሬት ኩታ ገጠም ስርአትን በመተግበር ከመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለሚተገበረው ሁለንተናዊ ተግባር እንደ ጂአይዜድ ያሉ አጋር አጋዥ አካላትና የግብርና ሚኒስቴር ትልቅ አበርክቶ ስለማድረጋቸውም አቶ ኡስማን አመላክተዋል።
የመሬት አጠቃቀም ደንብ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ በተደረገባቸው አካባቢዎች ከተበጣጠሰ አሰራር ይልቅ የተቀናጀ የመሬት ኩታ ገጠም ማሳን እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ዛሬ ላይ በክልላችን በሁለት ወረዳዎች ላይ በውስን ቀበሌዎች የተጀመረው የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ስርአት ውጤታማነቱን በተግባር በማረጋገጥ ነገ ላይ በሁሉም አካባቢዎች ላይ ለማስፋት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አቶ ኡስማን አስረድተዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚጎዳው የመሬት መከፋፈል እንደሆነ ያነሱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አልያ ሽኩር፤ ችግሩንም ለመፍታት የፖሊሲና የአዋጅ አካል በማድረግ በሙከራ ደረጃ በክልሉ በተመረጡ ሁለት ወረዳዎች እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ይህም አርሶ አደሩ ካለው የመሬት ሀብት ማግኘት ያለበትን ከፍተኛ ጥቅም እንዲያገኝ ያስችላል።
በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስራ አስፈፃሚ የመሬት ህግ ባለሙያ አበባው አበበ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የተቀናጀ የመሬት ኩታ ገጠም አሰራር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው አመላክተዋል።
ቀጣይነትና ዘላቂነት ያለው የመሬት አጠቃቀም ስርዓትን መከተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ማሳን ኩታ ገጠም የማድረግ ስራ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የገለፁት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የርዕሰ መስተዳድሩ የህግ ጉዳዮች ምክትል አማካሪ ወ/ሮ መቅደስ ማቲዮስ፤ በመንግስት በጀት በተሰሩ መሰረተ ልማቶች ላይ ግን አስገዳጅነት እንዳለው አስረድተዋል።
ለዚህ መመሪያና ደንብ ውጤታማነትና የምግብ ሉአላዊነት መረጋገጥ እንደ ክልል ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ: ረዚቃ ተመስገን – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የምርት ብክነት መከላከል እንዳለበት ተገለፀ
በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሰብላቸውን በህብረት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገለጹ