አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የምርት ብክነት መከላከል እንዳለበት ተገለፀ

አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የምርት ብክነት መከላከል እንዳለበት ተገለፀ

አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የምርት ብክነት መከላከል እንዳለበት የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ።

በዞኑ በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 180 ሺህ 29 ሄክታር ማሳ ከ8 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱም ተገልጿል።

የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወ/ጊዮርጊስ እንዳሉት፤ በዞኑ በመኸር እርሻ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዞኑ በመኸር እርሻ 180 ሺህ 29 ሄክታር መሬት በተለያዩ  የሰብል አይነቶች በዘር መሸፈኑንና ከዚህም ውስጥ 8 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በቆላማ አከባቢዎች ምርት ለመሰብሰብ መድረሱን የገለጹት አቶ ሳምሶን፤ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ እና በተለያዩ አደረጃጀቶች ታግዞ መሰብሰብ እንዳለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በየደረጃው እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በኩታ ገጠም የተዘሩና ማሽነሪ ለማስገባት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን በኮምባይነር  ለመሰብሰብ እንደ ዞን  ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ይህም ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ኮምባይነር ለማግኘት በደላላ በኩል የሚያደርገውን እንግልት የሚያስቀር መሆኑን ገልፀው፤ ምርት ለመሰብሰብ በደረሰበት አከባቢ ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሰራ አክለዋል።

አርሶአደሩ ሌሎች አደረጃጀቶችንም በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ከሚችለው የምርት ብክነት መከላከል እንዳለበትም አቶ ሳምሶን አሳስበዋል።

በዞኑ በአሁን ወቅት የበቆሎ ሰብል በተሰበሰበበት ከ2 ሺህ 700 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ በጸደይ እርሻ በሽንብራ ሰብል መሸፈኑንም ገልጸዋል።

በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት የደረሱ ሰብሎች ፈጥኖ እንዲሰበሰቡ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ ዕድሮችና ሌሎች ማህበራዊ መሰረቶችም እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በጋራ ሆኖ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ማበርከት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

 ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን