በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማሳደግና ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን በዳውሮ ዞን የኢሠራ ባሌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በከተማው በተለያዩ ማህበር የተደራጁ ወጣቶች በአንፃሩ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀው፤ የመብራት መቆራረጥ ለሥራቸው እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱ ለመፍተሄው እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡
ወጣት አፈወርቅ አበራ ከዛሬ 6 ዓመት በፊት በ69 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል አምስት ሆነው በከባድና ቀላል የመኪና ጋራጅ ስራ መሰማራታቸውን አስታውሶ፤ በሥራቸው ውጤታማ በመሆናቸው ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እና 600 ሺህ ብር ካፒታል በማፍራታቸው ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆኑን ገልጿል።
ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸው ለራሳቸው ሀብት ከማፍራት ባለፈ ለሌሎች የስራ እድል መፍጠራቸውንም አያይዞ አንስቷል።
ወጣት ዳኛቸው ወሰን እና ፍሰሀ ፍሬሁን የተባሉ በከተማ ግብርና እና የዶሮ ጫጩት ማርባት ማህበር የተደራጁ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ በስራቸው ውጤታማ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በሁለት የተለያዩ ማህበር አምስት ሆነው በመደራጀት ከ50 እሰከ 100 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በጀመሩት ሥራ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ጠቅሰው፤ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠራቸው ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህን ወጣቶች ጨምሮ ሌሎች በተለያዩ ዘርፎች የተደራጁ ወጣቶች በአከባቢው የሚከሰተው ተደጋጋሚ የመብራት መቆራረጥ ለስራችን እንቅፋት እየሆነ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ለመፍትሄው ቢሰሩልን መልካም ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የኢሠራ ባሌ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዝ ዩኒቲ አስተባባሪ አቶ ፈቃዱ ጌታቸው በአንፃሩ፤ በከተማ ግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
በከተማው በሶስቱ ዘርፎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው አብዘኞቹ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ሙያዊ የድጋፍና ክትትል ስራዎች መሰራቱ አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ ማገዙን አስረድተዋል።
የኢሠራ ባሌ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዝ፣ ግብርና፣ መንገድና ትራንስፖርት፣ ህብረት ስራ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አፈወርቅ አለሙ በበኩላቸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከ1 ሺህ 300 በላይ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፤ 645 ልየታ በማደረግ ከ130 በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል በመፍጠር ወደሥራ ማስገባታቸውን ተናግረዋል።
ለወጣቶቹ የመስሪያና መሸጫ ቦታ ከማመቻቸት ባለፈ የገበያ ትስስር በመፍጠር እና የድጋፍና ክትትል ስራ በመስራት ውጤታማነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
አቶ አፈወርቅ አክለውም ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልፀው፤ ወጣቶቹን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከኢሠራ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢሠራ ባሌ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ አባተ አበራ፤ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ስራ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የተነሳው የመብራት መቆራረጥ ችግር በአብዘኞች የስራ ዘርፎች እንቅፋት እየሆነ መመጣቱን ተቀብለው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥረት እየተደረገ ሰለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
አዘጋጅ፡ አፈወርቅ ኦሹ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
የመሬት ኩታ ገጠም የአስተራረስ ስርአትን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገለፁ
አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የምርት ብክነት መከላከል እንዳለበት ተገለፀ
በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሰብላቸውን በህብረት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገለጹ