በሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት መዳናቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ለማግኘት በመጡበት ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ

በሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት መዳናቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ለማግኘት በመጡበት ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ

የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ በማዘመን ህብረተሰቡን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

በሆስፒታሉ ለህክምና አገልግሎት በመጡበት አግኝተን ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች ወይዘሮ ትዕግሥት አባይነህ እና ወይዘሮ አበራሽ ማርቆስ በሆስፒታሉ ቀዶ ህክምና እንደተደረገላቸው የጠቆሙ ሲሆን ሌላኛው የአገልግሎት ተጠቃሚ አቶ አለማየሁ ዘለቀም ከዚህ ቀደም ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት በመሄድ ለተለያዩ እንግልቶች ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተቋሙ ውስጥ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱንና በተሰጣቸው የጤና አገልግሎትም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የህክምና ስራ የሰው ልጅ ህይወት አዳኝ ተግባር በመሆኑ ለታካሚዎች ተገቢውን የህክምና አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን ያሉት የሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ዮሴፍ ታፈሰ ናቸው።

የሆስፒታሉን ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ስራ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

የሆስፒታሉ የማህፀንና ፅንስ እስፔሻሊስት ዶክተር ተመስገን ኦርሽሶ በበኩላቸው፤ “አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም” የሚለውን የህክምና መርህ በመከተል በሆስፒታሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለእናቶች ህክምና ልዩ ትኩረት በመስጠት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የሆስፒሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ በየነ፤ ሆስፒታሉ ለበርካታ የአጎራባች ዞኖችና ወረዳ ህዝቦች የተሻለ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ በማዘመን ህብረተሰቡ ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ማቴዎስ ሀደሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን