ታሪካዊና ጥንታዊው – ምሁር ኢየሱስ ገዳም

ታሪካዊና ጥንታዊው – ምሁር ኢየሱስ ገዳም

ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሀገራችን ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ነው።

በገዳሙ ውስጥ የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ዮዲት ጉዲት በፊት በ804 ዓ.ም እንደተተከለ ይነገራል፡፡

ኢየሱስ ገዳም በጉራጌ ዞን በምሁር አክሊል ወረዳ ከአዲስ አበባ በ207 ኪሎ ሜትር፣ ከወልቂጤ በ52 ኪሎ ሜትር፣ ከወረዳው ዋና ከተማ ሐዋርያት 3 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን ምስራቅ በኩል ይገኛል፡፡

ምሁር ኢየሱስ ገዳም በገዳምነት የተገደመው በታላቁ አባት አቡነ ዜና ማርቆስ በ13ኛ ክፍለ ዘመን (በ1250 ዓ.ም) መሆኑን መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡

የገዳሙ ምክትል አስተዳዳሪ አባ ኤልሳ በርታ በገዳሙ ስለሚገኙ በርካታ ዘመናት ያስቆጠሩ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ሰነዶችና ስለ ገዳሙ አጠቃላይ ታሪካዊ ዳራና አሁናዊ ሁኔታ ለጋዜጠኞች ቡድን ገለጻ አድርጎዋል።

ከ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ከ804 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ-ክርስትያንነት ሲያገለግል ቆይቶ በገዳምነት የተመሰረተው (የተገደመው) በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፃድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ መሆኑን ገልፀዋል።

በገዳሙ ሰባት የጉባኤ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህም የንባብ፣ ቅዳሴ፣ ዜማ፣ መጽሐፍ ትርጓሜ፣ አቋቋም፣ የቅኔና በገና ቤት ሲሆኑ የአብነት ተማሪዎች በእነዚህ የጉባዔ ቤቶች ትምህርት እንደሚያገኙ ገልፀዋል።

በዚሁ ጥንታዊ ገዳም ስር አቡነ ዜናማርቆስ ለ40 ዓመት የፀለዩበት በውስጡ ጸበልና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቅርሶች ያሉበትና በተፈጥሮ ደኖች የተከበበው የከሬብ ዋሻ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ገዳሙ በተለያዩ ጊዜያት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና ቱሪስቶች የሚጎበኙት ታሪካዊና ድንቅ ስፍራ ሲሆን በተለይም የአብይ ፆም እኩሌታ/ደብረዘይት/ ምዕመናን ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በመምጣት በበገናና በፀሎት የሚያሳልፉበት ስፍራ እንደሆነም ምክትል አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ገብሬ ገዳሙ ከሀይማኖታዊ ትውፊትነት ባሻገር የቱሪስት መስህብ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ገዳሙን ለማስተዋወቅና የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ለማስቻል ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ መለሰች ዘለቀ