ብሩኖ ፈርናንዴዝ የማንቸስተር ዩናይትድን የኮንትራት ማራዘሚያ ጥያቄ ውድቅ አደረገ

ብሩኖ ፈርናንዴዝ የማንቸስተር ዩናይትድን የኮንትራት ማራዘሚያ ጥያቄ ውድቅ አደረገ

የማንቸስተር ዩናይትድ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ በኦልድ ትራፎርድ የሚያቆየውን ሁለተኛ የኮንትራት ማራዘሚያ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ተሰምቷል።

ፖርቹጋላዊው አማካይ ባለፈው ክረምት ክለቡ ያቀረበለትን የመጀመሪያ የውል ማራዘሚያ ጥያቄ አለመቀበሉ ይታወሳል።

የክለቡ አመራሮች በቅርቡ የተሻሻለ ጥቅማጥቅም ያካተተ ሁለተኛ ጥያቄ ቢያቀርቡለትም፣ ፈርናንዴዝ አሁንም በቀረበለት የደመወዝ መጠን እና የኮንትራት ቆይታ ባለመርካቱ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።

የ32 ዓመቱ የመሃል ሜዳ ተጫዋች አሁን ያለው ኮንትራት በያዝነው የውድድር ዘመን መጨረሻ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ከእንግሊዝ ውጭ ካሉ ክለቦች ጋር በነፃ ዝውውር ለመዘዋወር ቅድመ-ስምምነት መፈራረም ይችላል።

ይሁን እንጂ ማንቸስተር ዩናይትድ የተጫዋቹን ኮንትራት ለተጨማሪ አንድ ዓመት በራሱ ውሳኔ የማራዘም እና በነፃ እንዳይለቅ የማገድ መብት በውሉ ላይ አለው።

ይህ የኮንትራት አለመግባባት የተከሰተው ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክን ካሰናበተ በኋላ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖን በዋና አሰልጣኝነት ለመሾም በተቃረበበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል።

ምንም እንኳን ሁለቱ ወገኖች እስካሁን ስምምነት ላይ ባይደርሱም፣ ንግግሩ ሙሉ በሙሉ እንዳልተቋረጠና ክለቡ ቁልፍ ተጫዋቹን ለማቆየት በቀጣይ ተጨማሪ ድርድሮችን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ብሩኖ ፈርናንዴዝ በጥር 2020 ከስፖርቲንግ ሊዝበን ማንቸስተር ዩናይትድን ከተቀላቀለ በኋላ በቡድኑ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ሲሆን በርካታ የቡድንና የግል ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ወደ ክለቡ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ውድድሮች ከ80 በላይ ግቦችን በማስቆጠርና ከ70 በላይ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት ሞተር ሆኖ ይገኛል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ