20 የሊግ ዋንጫዎችን በሦስት አሰልጣኞች ብቻ

20 የሊግ ዋንጫዎችን በሦስት አሰልጣኞች ብቻ

ማንችስተር ዩናይትድ በታሪኩ ያሳካቸውን 20 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ (የቀድሞው ፈርስት ዲቪዥን) ዋንጫዎች ያነሳው በሦስት አሰልጣኞች ብቻ ነው።

የክለቡ የቀድሞ ኮከቦች ፖል ስኮልስ እና ኒኪ በት ከእነዚህ አሰልጣኞች መካከል ሁለቱን በቀላሉ ቢያውቋቸውም፣ ሦስተኛው ስም ግን ግራ አጋብቷቸዋል።

“ማን?!” ሲል ስኮልስ በመገረም ሲጠይቅ፣ ኒኪ በት በበኩሉ “ስሙን ሰምቼው አላውቅም” ብሏል።

ስኮልስ እና በት ያላወቁት ይህ አሰልጣኝ ኤርነስት ማንግናል ይባላል።

ማንግናል እ.ኤ.አ በ1907-08 እና በ1910-11 የውድድር ዘመናት ለማንችስተር ዩናይትድ የመጀመሪያዎቹን ሁለት የሊግ ዋንጫዎች ያስገገኙ አሰልጣኝ ናቸው።

ከዚያ በኋላ ሰር ማት ባዝቢ አምስት፣ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ደግሞ 13 የሊግ ዋንጫዎችን በማከል የክለቡን ታሪክ ጽፈዋል።

ታሪካዊ ባላንጣቸው ሊቨርፑል 20 የሊግ ዋንጫዎችን በ10 የተለያዩ አሰልጣኞች (ከቶም ዋትሰን እስከ አርኔ ስሎት) ሲያሳካ፣ ዩናይትድ ግን ከ20 ዋንጫዎቹ 18ቱን ያገኘው በሁለት አሰልጣኞች (ባዝቢ እና ፈርጉሰን) ብቻ ነው።

እነዚህ ሁለት አሰልጣኞች ከዋንጫ ባለፈ የክለቡን ማንነት፣ ባህል እና የአሸናፊነት ስነ-ልቦና የገነቡ ናቸው።

ይህ ደግሞ አንድ ትልቅ ጥያቄ ያስነሳል፤ “ማንችስተር ዩናይትድ በሁለት ግለሰቦች አመራር ስር ሦስት እና ከዛ በላይ የሊግ ዋንጫዎችን በማንሳቱ፣ ያለ እንደዚህ አይነት ‘መሲህ’ ስኬታማ መሆን ተስኖት ይሆን?” የሚል።

ክለቡ ከባዝቢ በኋላ ፈርጉሰንን ለማግኘት 17 ዓመታትን ጠብቋል፤ አሁን ደግሞ ሦስተኛውን አዳኝ በማፈላለግ ላይ ይገኛል።

ማት ባዝቢ በ1945 ዩናይትድን ሲረከብ ክለቡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ኦልድ ትራፎርድ ፈራርሶበት ጨዋታዎቹን በማንችስተር ሲቲ ሜዳ (ሜይን ሮድ) የሚያደርግ ደካማ ክለብ ነበር።

ባዝቢ ግን በወቅቱ ወጣቶችን የማሳደግ እና በአውሮፓ ተፎካካሪ የመሆን ግልጽ ራዕይ ይዞ መጣ።

“የባዝቢ ህጻናት” (Busby Babes) የተሰኘው ድንቅ ቡድን የዚህ ራዕይ ውጤት ነበር።

በፈረንጆቹ 1958 የደረሰው የሙኒክ የአውሮፕላን አደጋ ስምንት ተጫዋቾችን ሲነጥቅ ባዝቢም ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር። ሆኖም አደጋው ክለቡን ከማጥፋት ይልቅ የዳግም ትንሳኤው አካል ሆነ።

ባዝቢ ቡድኑን እንደገና በመገንባት በጆርጅ ቤስት፣ ዴኒስ ሎው እና ቦቢ ቻርልተን በመታገዝ ከአደጋው 10 ዓመታት በኋላ በ1968 የአውሮፓ ዋንጫን ያነሳ የመጀመሪያው የእንግሊዝ ክለብ እንዲሆን አደረገው።

የቀድሞ የዩናይትድ አካዳሚ ተጫዋች አሮን በርንስ እንደሚለው፣ በክለቡ ውስጥ ታሪክ በግድግዳ ላይ የተሰቀለ ስዕል ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የሚኖር እውነታ ነው። በርንስ “ፈርጉሰን የራሳቸውን እሴቶች ገንብተዋል፤ ነገር ግን የገነቡት በሰር ማት ባዝቢ መርሆዎች ላይ ነው” ይላል።

ከባዝቢ መልቀቅ በኋላ አምስት አሰልጣኞች ቢፈራረቁም ዩናይትድ ለ26 ዓመታት የሊግ ዋንጫ ሳያይ ቆይቷል።

በህዳር 1986 ከስኮትላንድ የመጣው አሌክስ ፈርጉሰን ይህንን ታሪክ ቀየረው። ፈርጉሰን እንደ ባዝቢ ሁሉ ወጣቶችን በማብቃት (እንደ ዴቪድ ቤካም፣ ስኮልስ እና ጊግስ ያሉትን የ92ቱን ትውልድ በማውጣት) እና ቡድኑን በየጊዜው በማደስ በ1993 የ26 ዓመታት የዋንጫ ጥማትን አስቆመ፤ በ1999 ደግሞ ታሪካዊውን የሦስትዮሽ ዋንጫ (Treble) አሳካ።

የፈርጉሰን ስኬት ሚስጥር ታክቲክ ብቻ ሳይሆን የፈጠሩት ባህል ነበር።

ጋሪ ኔቪል በመጽሐፉ ላይ እንደገለጸው፣ ቡድኑ በግለሰብ ብቃት ላይ ቢመሰረትም “ጨዋታውን እናሸንፈዋለን” የሚል የጋራ መንፈስ ነበረው።

ሮይ ኪን በበኩሉ፣ አዲስ ተጫዋቾች (ለምሳሌ ዲዬጎ ፎርላን) ሲቸገሩ ነባር ተጫዋቾች ተረባርበው እንደሚደግፏቸው ይመሰክራል።

ፈርጉሰን “ከተጋጣሚያችን በላይ ጠንክረን ያልሰራንበት ደቂቃ፣ ማንችስተር ዩናይትድ መሆናችን ያበቃል” የሚል የማይናወጥ መርህ ነበራቸው።

ፈርጉሰን ለረዳት አሰልጣኞቻቸው እና ለህክምና ባለሙያዎች ሙሉ ነጻነት ይሰጡ ነበር። ተጫዋቾችን ከቋሚ አሰላለፍ ውጭ ሲያደርጉም ለእያንዳንዱ ተጫዋች በግል ምክንያቱን ያስረዱ ነበር።

በዚህም ምክንያት በጨዋታ ቀን የሚናገሯቸው ጥቂት ቃላት በተጫዋቾች ዘንድ ትልቅ ክብደት እና ተሰሚነት ነበራቸው።

ዛሬም ማንችስተር ዩናይትድ ያንን የቀድሞ ክብሩን ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት፣ የሰር ማት ባዝቢ እና የሰር አሌክስ ፈርጉሰንን ፈለግ የሚከተል አዲስ መሪ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ