የአርቴታ አዲስ ስልት ለዲክላን ራይስ ምን አበረከተ?

የአርቴታ አዲስ ስልት ለዲክላን ራይስ ምን አበረከተ?

አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ካከናወናቸው 9 ጨዋታዎች 8ቱን አሸንፎ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሆኖ ሲመራ፣ ከስኬቱ ጀርባ ትልቁን ድርሻ እየወሰደ የሚገኘው የመሐል ስፍራ ተጫዋቹ ዲክላን ራይስ ነው።

የቀድሞው “የመሃል ሜዳ መልህቅ” አሁን ላይ ሚናው ተቀይሮ የግብ እድል ፈጣሪ እና የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ ሆኗል።

በአርሰናል ቤት አስደናቂ ብቃትን እያሳየ የሚገኘው የ27 ዓመቱ አማካይ፤ ባለፈው እሁድ ሊቨርፑልን ባሸነፉበት ጨዋታ የጨዋታው ምርጥ ተጫዋች በመባል ተሸልሟል።

አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድኑን በብሩኖ ጊማራኤሽ ማጠናከሩ ለራይስ ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል።

በተጨማሪም ወጣቱ ተጫዋች ማይልስ ሉዊስ – ስኬሊም ከእሱ ጋር በመፈራረቅ መጫወት መቻሉ ራይስ ከወትሮው በተለየ መልኩ ወደፊት ገፍቶ በማጥቃት እንዲሳተፍ አስችሎታል።

የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት ከራይስ ጋር ያደረጉት ወሳኝ ንግግር የዚህ ለውጥ መሰረት ነው።


አርቴታ ለተጫዋቹ ከአሁን በኋላ የቡድኑ “መልህቅ” (የተከላካይ አማካይ) ብቻ እንዳልሆነ፣ ከእሱ ከዚህ በላይ የጎል አስተዋጽኦ እንደሚፈልጉ ነግረውታል።


ራይስ ከማች ኦፍ ዘ ዴይ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ውይይቱ ሲናገር “የውድድር ዘመኑን የጀመርኩበት ቦታ ለኔ በጣም የሚመቸኝ ነው። በ8 ቁጥር ፣ በ6ቁጥር እንዲሁም በሜዳው መሃል ባሉ ሁሉም ስፍራዎች ተጫውቻለሁ። ነገር ግን ከውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ወቅት ከአሰልጣኙ ጋር ያደረግነው ንግግር የተሻለ ብቃት እንዳስመዘግብ አድርጎኛል፤ አሁንም ከዛ በላይ መስራት እንደሚችል አሰልጣኙ ያምናሉ” ብሏል።

ተጫዋቹ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ እጅግ ድንቅ ብቃትን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን፣ በሊጉ 5 ግብ የሆኑ የመጨረሻ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ከየትኛውም ተጫዋች ቀዳሚ ሆኖ ይገኛል።

ከዚህም በላይ ሁሉም አሲስቶች የተገኙት በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ (Open play) መሆኑ አዲሱ የሜዳ ላይ ሚናው ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።

ባለፈው የውድድር ዘመን ለክለቡ እና ለሀገሩ በአጠቃላይ 55 ጨዋታዎችን ያደረገው ራይስ፤ በጡንቻ ህመም እና ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር በ2026ቱ ዓለም ዋንጫው እስከ ግማሽ ፍፃሜ በመዘለቁ ምክንያት ከፍተኛ ድካም አስተናግዶ ነበር።

በዘንድሮው ዓመት ግን ብሩኖ ጊማራኤሽ ወደ ክለቡ መምጣት ለራይስ በኢኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች እረፍት እንዲያገኝ ያስቻለው ሲሆን፣ በብሔራዊ ቡድኑም በመስከረም ወር የሀገራት የጨዋታ ሰሞን በተመሳሳይ እንዲያርፍ ተደርጓል።

ይህ ብልሃት የተሞላበት የአስተዳደር ውሳኔ ራይስ በአካልም በስነ-ልቦናም ታድሶ እንዲመለስ አድርጎታል።
 
ዴክላን ራይስ በሜዳ ላይ ያለው ስኬት በውል ማራዘም ውይይቶችም ላይ ተንጸባርቋል።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተጫዋቹ በረጅም ጊዜ እቅዳቸው ውስጥ መካተቱን ገልጸው፣ አዲስ ውሉን ለመፈራረም ከስምምነት ላይ መደረሱ የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

አርሰናል በሊጉ አናት ላይ ተቀምጦ ወደፊት እየገሰገሰ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የዲክላን ራይስ አዲስ ሚና እና ብቃት የመድፈኞቹ ዋና የድል ቁልፍ ሆኖ ቀጥሏል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ