የማሠልጠኛ መሣሪያዎችን በራስ ባለሙያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲበቁ መስራት ይገባል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ

የማሠልጠኛ መሣሪያዎችን በራስ ባለሙያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲበቁ መስራት ይገባል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ

በተለያየ ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑ የማሠልጠኛ መሣሪያዎችን በራስ ባለሙያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲበቁ መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የማሠልጠኛ መሣሪያዎች ብልሽትን በራስ ባለሙያ ለመጠገን የሚያስችል የባለሙያዎች ሥልጠና  በታርጫ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።

በስልጠናው የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፤ የሥራና  ክህሎት ማሰልጠኛ ተቋማት በርካታ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የሚገኙበት መሆናቸውን ገልፀው፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ ከፍተኛ የሀገር ሀብት ወጥቶባቸው ከውጪ ጭምር የሚገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በርካታ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ እነዚህ ከፍተኛ የማሠልጠኛ መሣሪያዎች ግን በትናንሽ ብልሽቶች ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ ሆነው እንደሚታዩ ገልፀዋል።

በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑ እነዚህን የስልጠና መሣሪያዎች የየተቋሙ ባለሙያዎችን ክህሎት በማሳደግ ተጠግነው ለአገልግሎት ማብቃት እንደሚገባ አቶ ፋንታሁን አስረድተዋል።

የስልጠናው ዓላማ በትናንሽ ብልሽት ምክንያት ከሥራ ውጪ የሆኑ የማሠልጠኛ መሣሪያዎችን በሠለጠኑ ባለሙያዎች ለሥራ እኖዲበቁ ማስቻል ነው ብለዋል።

በኢትዮጽያ የቴክኒክ ልህቀት ኢንስቲትዩት የሐዋሳ ካምፓስ ከፍተኛ ባለሙያዎች በታርጫ ከተማ እየተሰጠ በሚገኘው የመሣሪያዎች ጥገና ሥልጠና፤ በክልሉ ከሚገኙ ኮሌጆች የተወጣጡ አሰልጣኝ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን ለቀጣይ 4 ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥም ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን