የህግ ባለሙያዎችን ብቃትና ክህሎት ማጎልበት ለውጤታማ የፍትህ አገልግሎት ወሳኝ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
የህግ ባለሙያዎችን ብቃትና ክህሎት ማጎልበት ለውጤታማ የፍትህ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ ገለጹ።
የክልሉ ፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት በክልሉ ለሚገኙ የህግ ባለሙያዎች የሥራ ላይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ማስጀመሪያ መድረክ አካሂዷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ለአምስተኛ ዙር የስራ ላይ ሰልጣኞች ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ እንደተናገሩት፤ ሰልጣኞች ዕውቀታቸውን፣ ብቃታቸውንና ሙያዊ ስነ-ምግባራቸውን ማጎልበት ለፈጣንና ውጤታማ የፍትህ አሰጣጥ የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በሕግና በተግባር አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍና አዳዲስ ሕጎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ብቁ ባለሙያዎች መሆን እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
አያይዘውም ባለሙያዎች ወጥነትና ተገማችነት ያለው ፍትህ ለመስጠት አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በአግባቡ መረዳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አድማሱ መንግስቱ እንዳሉት፣ ተቋሙ በክልሉ የፍትህ ተቋማት አሠራር፣ አደረጃጀትና የሕግ ማዕቀፎች ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድ እንዲሁም ስልጠናዎችን በመስጠት ለፍትህ ሥርዓቱ መሻሻል አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
የፍትህ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ፣ ሕዝቡም ፈጣንና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የሕግ ባለሙያዎች ሙያዊ ብቃታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በስልጠና ማሳደግ ተገቢ መሆኑን አቶ አድማሱ አስገንዝበዋል።
የሳውላ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ማርቆስ ማኖታ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ሰልጣኞች የሚኖራቸው ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በስልጠናው ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ሪጂዮፖሊስ ከተሞች የተውጣጡ 115 ዳኞች፣ ዐቃቤያነ ሕግ፣ ረዳት ዳኞች እና ሪጅስትራሎች የሚሳተፉ ሲሆን ለአራት ወራት እንደሚቆይ ተገልጿል።
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ በሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ተግባራት ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
በመድረኩ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንዷለም አምባዬ፣ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ታደስ፣ የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አድማሱ መንግስቱ፣ የአቅም ግንባታና ፖሊስ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ፕሮፈሰር ታከለ ታደሰ፣ የማረሚያ ኮሚሽን ኮምሽነር ብርቱካን መንግስቱ፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ዋና፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሰልጣኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት መሠራት እንዳለበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ አሳሰቡ
ሁሉንም ተግባራት የፖሊስን ክብር በሚያስጠብቅ መንገድ ማከናወን እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ተናግረዋል
ያሉንን የገቢ አማራጮች አሟጦ በመጠቀም የሕዝቡን እያደገ የመጣ የልማት ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባ የጋሞ ዞን አስተዳደር አሳሰበ