በኮሬ ዞን የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመረው የክትባት ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአባሰንጋ በሽታ መከላከያ ክትባት ካልተሰጠ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ እንስሳትን የሚጨርስ አደገኛ በሽታ በመሆኑ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እንስሳቶቻቸውን በወቅቱ እንዲያስከትቡ የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ ጥሪ አቀረበ።
የአካባቢው አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች በበኩላቸው የቤት እንስሳቶቻቸው የሕይወታቸው መሠረትና የሀብታቸው ምንጭ በመሆናቸው፣ ወቅቱን የጠበቀ የእንስሳት ጤና ክትባትና የሕክምና አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
በኮሬ ዞን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቀንድና የጋማ ከብቶች የሚገኙ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከዶሮ በስተቀር ለሁሉም እንስሳት አደጋ የሚደቅነው የአባሰንጋ በሽታ ለመከላከል የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል።
ከዞኑ ዶርባዴ ቀበሌ አቶ ደጀኔ ደሳለኝ እና አቶ ደመላሽ ደረሱ የተባሉ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እንደተናገሩት፤ የክትባት አገልግሎቱ በተገቢው መንገድ መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ የእንስሳቶቻቸው ጤንነት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በተመሳሳይ የጋሙሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶና ከፊል አርብቶ አደር መከሩ ዱቤ፣ የክትባቱን አስፈላጊነት በመረዳት እንስሳቶቻቸውን ሳያቋርጡ እንደሚያስከትቡ ገልጸዋል።
አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮቹ አክለውም፣ የአባሰንጋ ክትባትን ጨምሮ ለገንዲ ዝንብ መከላከያ የሚሆን የኬሚካል ርጭት እንዲሁም የእንስሳትን እግርና አፍ የሚያቆስል በሽታን የሚከላከሉ መድኃኒቶች በየወቅቱ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
የእንስሳት ሕክምና ባለሙያው አቶ ፈይሳ ፋንታሁን እንደገለጹት፤ የአባሰንጋ በሽታ በከብቶች ላይ ከፍተኛ ደም ማፍሰስን የሚያስከትልና በክትባት ካልተከላከልነው በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙ እንስሳትን ሕይወት የሚቀጥፍ አደገኛ ገዳይ በሽታ ነው።
በኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ቡድን መሪ ዶክተር ዓለሙ ጥላሁን በበኩላቸው፤ እንስሳት ሙሉ ጤንነታቸው ተጠብቆ አመርቂ ምርት እንዲሰጡ በዓመት ከ6 እስከ 8 የሚደርሱ ልዩ ልዩ የመከላከያ ክትባቶች እንደሚያስፈልጓቸው ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት የአባሰንጋ በሽታን ለመግታት ያለመ የክትባት ዘመቻ ተጠናክሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ዶክተር ዓለሙ አክለው እንደገለጹት፤ የገንዲ ዝንብ መከላከያ ቀደም ሲል በአጋር ድርጅት በኩል ሲሰጥ የነበረው ኬሚካል ርጭት በአሁኑ ወቅት መቋረጡን ገልጸው፣ ለአፍና እግር በሽታ የሚሆን የሕክምና መድኃኒት ዋጋ ውድ ቢሆንም በክትባት መከላከል እንደሚቻል አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጤናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የወላይታ ዞን አስተዳደር ገለጸ
በቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ የማህበረሰቡ እንግልት መቀነሱ ተገለፀ
የወባ ቅድመ መከላከል ስራ ውጤት እያስገኘ መምጣቱን በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ