ያሉንን የገቢ አማራጮች አሟጦ በመጠቀም የሕዝቡን እያደገ የመጣ የልማት ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባ የጋሞ ዞን አስተዳደር አሳሰበ

ያሉንን የገቢ አማራጮች አሟጦ በመጠቀም የሕዝቡን እያደገ የመጣ የልማት ጥያቄዎች መመለስ እንደሚገባ የጋሞ ዞን አስተዳደር አሳሰበ
‎
‎የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ100 ቀናት ዕቅድ የምክክር መድረክ በአርባምንጭ አካሂዷል።
‎
‎የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በመድረኩ ተገኝተው እንዳሉት፤ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በሥርዓትና በአሰራር ማዕቀፍ በመምራት፣ ወጪን በመቀነስና ያሉትን የገቢ አማራጮች አሟጦ በመሰብሰብ የሕዝቡን እያደገ የመጣ የልማት ፍላጎት መመለስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
‎
‎በዞኑ የሚገኙ አንዳንድ መዋቅሮች የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ በወቅቱ መክፈል እየተቸገሩ መሆኑን ያነሱት አቶ ገዛኸኝ፣ በየአካባቢው የሚገኙ ሀብቶችንና ፀጋዎችን በማልማትና በመጠቀም ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
‎
‎የመደመር መንግሥት ዋነኛ ዓላማ የሕብረተሰቡን ሕይወት መቀየር መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ የተፈጠረውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ያሻልም ብለዋል።
‎
‎ብልሹ አሠራሮችን ማረምና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራት እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ገዛኸኝ፤ በሥነ ምግባር ችግር ውስጥ በገቡ አካላት ላይ የተጀመረው የተጠያቂነት ርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
‎
‎በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ በመለየትና በማልማት ቀጣይነት ያለውና የተረጋጋ ገቢ ለመሰብሰብ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለፁት ደግሞ የጋሞ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ሀኪሜ አየለ ናቸው።
‎
‎አመራሩ ከተለመደው የገቢ አሰባሰብ አሠራር በመላቀቅ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን መፍጠርና በተግባር ማዋል እንዲሁም የውስጥ ወጪዎችን ለመሸፈን በትጋት መንቀሳቀስ እንደሚገባም አቶ ሀኪሜ አሳስበዋል።
‎
‎የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቶቤ፤ የሚሰበሰበው ገቢ በባንክ ሂሳብ ገቢ በማድረግና በተቀመጠው የፋይናንስ አሠራር መሠረት መመራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
‎
‎የገቢ ተቋማት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራትና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አቶ ቶማስ ገልጸዋል።

እንዲሁም የገቢ ዓይነቶችን በየወቅቱ ለይቶ በመገምገምና ተገቢውን አቅጣጫ በማስቀመጥ መምራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
‎
‎በምክክር መድረኩ የተሳተፉት አካላት፣ ገቢ ለሁሉም የልማት ሥራዎች መሠረት በመሆኑ ዘርፉን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
‎
‎በተጨማሪም ተግባራትን በሕግና በመመሪያ መሠረት መምራት፣ ያሉትን የገቢ አማራጮች አሟጦ መጠቀም፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በፍጥነት ማረም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
‎
‎በመድረኩ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
‎
‎ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን