ሁሉንም ተግባራት የፖሊስን ክብር በሚያስጠብቅ መንገድ ማከናወን እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ተናግረዋል

ሁሉንም ተግባራት የፖሊስን ክብር በሚያስጠብቅ መንገድ ማከናወን እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ተናግረዋል

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የ2019 በጀት ዓመት 2ኛ ዙር የ100 ቀናት እቅድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ በሁሉም ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ይገመገማሉ ብለዋል።

የፖሊስ ሪፎርምን ተግባራዊ ለማድረግ በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የክልሉ ፖሊስ ፋውንዴሽን እንደሚቋቋምና እስካሁን የነበሩ ችግሮች ተቀርፈው ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የፖሊስ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ለሀገራዊ ተልዕኮዎች ዝግጁ በመሆን ባለፈው ዓመት የተከናወነው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በሠላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በዚህ መድረክ በ2018 በጀት ዓመት የላቀ የሥራ ውጤት ላስመዘገቡ የፖሊስ ሠራዊት አመራሮችና አባላት እውቅና እና ሽልማት እንደሚበረከት ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ ተናግረዋል።

ለክልሉ ሠላም መከበር ዋጋ ለከፈሉ አካላት እውቅና መስጠት ለተሻለ ስራ እንደሚያነሳሳ ገልጸው፤ እውቅናው የማዕረግ እድገትን፣ ሽልማትን እና የእርከን ደረጃ እድገትን ያካትታል ብለዋል።

የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ሰላማዊና ለሁሉም ዘርፍ ስራዎች ምቹ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ለዚህ ውጤታማነት ክልሉን ላበቁ የፖሊስ ሠራዊት አባላትንና አመራሮችን አመስግነዋል።

እንደ ሀገርም እንደ ክልልም በርካታ ህዝባዊ ኹነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወኑ በማድረግና የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት ፖሊስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላት እውቅና መስጠትና ክፍተቶችንም ማረም ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።

ጥቃቅን ወንጀሎች እና ህዝብ ላይ ስጋት የሚፈጥሩ አካላት እንዳሉ ታውቆ ማስተካከያ እንዲደረግ አሳስበው፤ በትራፊክ ቁጥጥር ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ህገ-ወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድና የጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ በተደረጉ የቁጥጥር ስራዎች ውጤት ቢመዘገብም ተጨማሪ ስራዎችን ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም በጦር መሣሪያና በነዳጅ ዝውውር ላይ በሙያ ሥነ-ምግባር መሠረት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የፖሊስን ክብር በሚያስጠብቅ መንገድ መንቀሳቀስና ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ አንድነት፤ የስልጠና አሰጣጥን ማጠናከርና የአቅም ግንባታ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አዳዲስና ብቁ ዜጎች ወደ ፖሊስ ተቋም እንዲቀላቀሉ ማድረግና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የህግና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዳግም ዳንኤል፣ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች፣ የዞኖችና የወረዳዎች ፖሊስ አዛዦች እንዲሁም አመራሮች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን