«ዴክላን ራይስ በፕሪምየር ሊጉ የላቀውና አቻ የሌለው አማካይ ነው» ጃሚ ካራገር

«ዴክላን ራይስ በፕሪምየር ሊጉ የላቀውና አቻ የሌለው አማካይ ነው» ጃሚ ካራገር

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት አርሰናል ሊቨርፑልን ባሸነፈበት ተጠባቂ ጨዋታ የሰሜን ለንደኑ ክለብ ድንቅ የቡድን መንፈስ ያሳየ ቢሆንም፣ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ግን የክለቡ ውድ አማካይ ዴክላን ራይስ ያሳየው አስደናቂ ብቃት ነው።

የቀድሞው የሊቨርፑል የተከላካይ መስመር ተጫዋች እና አሁን በስካይ ስፖርት የእግርኳስ ስፖርት ተንታኝ የሆነው ጃሚ ካራገር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጠው አስተያየት፣ ዴክላን ራይስን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው (World Class) ተጫዋች ሲል አሞካሽቶታል።

ራይስ በዚህ ጨዋታ አርሰናል ከሚፈልገው በላይ ፍጹም የሆነ የሜዳ ላይ ብቃት ያሳየ ሲሆን፣ ካይ ሀቨርትዝ አሸናፊዋን ግብ ሲያስቆጥር ድንቅ ኳስ አመቻችቶ ማቀበሉ ብቻ ሳይሆን በአርሰናል የመሃል ሜዳ ላይ ጠንካራ የመከላከል መሰረት በመሆን የቡድኑ መሪ መሆኑን አስመስክሯል።

ሊቨርፑል በጨዋታው መጨረሻ ላይ አርሰናል ላይ ከፍተኛ ጫና በፈጠረበት ወቅት፣ ራይስ ወሳኝ ኳሶችን በማቋረጥ የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል።

በጨዋታው 62 ጊዜ ኳስ በመንካት ከአርሰናል ተጫዋቾች ቀዳሚው የነበረው ራይስን አስመልክቶ ካራገር ሲናገር«ዴክላን ራይስ አርሰናል ከነበሩት ታላላቅ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች አንዱ ነው። ክለቡ ቀደም ሲል አስደናቂ አማካዮች እንደነበሩት ይታወቃል፤ ራይስ ግን ከእነዚያ ምርጦች ጋር አብሮ የሚሰለፍ ነው» ብሏል።

ካራገር አክሎም«በአሁኑ ሰዓት እርሱ በፕሪምየር ሊጉ ውስጥ በሰፊ ልዩነት በአንደኝነት ላይ የሚገኝ ምርጥ የመሃል ሜዳ ተጫዋች ነው። ይህ ደግሞ በጭራሽ ክርክር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም» ሲል የራይስን የበላይነት አፅንዖት ሰጥቶ ገልጿል።

የዴክላን ራይስ አስደናቂ ብቃትና የመሪነት ብቃት ለአርሰናል የዋንጫ ተፎካካሪነት ትልቅ መተማመንን የፈጠረ ሲሆን፣ ተጫዋቹ ለቡድኑ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን እያገኘ ይገኛል።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ