“በአሰልጣኝነት አንፊልድ ላይ ማሸነፍ ከምንም በላይ ልዩ ስሜት አለው” ሚኬል አርቴታ
አርሰናል ከ14 ዓመታት ከረጅም የጥበቃ ጊዜ በኋላ በአንፊልድ ሊቨርፑልን ማሸነፍ መቻሉን ተከተሎ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ደስታቸውን ገልፀዋል።
የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድናቸው በሊቨርፑል ሜዳ አንፊልድ ያመዘገበውን ታሪካዊ ድል በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፤ በአንፊልድ ማሸነፍ በተለይ በአሰልጣኝነት ደረጃ እጅግ በጣም ልዩ እና የላቀ ስሜት የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
አርሰናል ለበርካታ ዓመታት ያልተወጣውን ይህንን ትልቅ ተልዕኮ ማሳካት መቻሉ ትልቅ ኩራት እንደሆነ የገለጹት አርቴታ፣ ጨዋታው የተካሄደበት ሁኔታ እና ቡድኑ የነበረበት መንፈስ ድሉን የበለጠ ጣፋጭ እንዳደረገው ጠቁመዋል።
አርቴታ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት መግለጫ”በአሰልጣኝነት ደረጃ አንፊልድ ላይ ማሸነፍ ከምንም በላይ ይለያል፤ ምክንያቱም ይህንን ድል ካየን ረጅም ጊዜ ሆኖን ነበር። ድሉ በእርግጥም እጅግ የሚያስፈልገን ነበር። ከፍሊትዉድ ሽንፈት በኋላ ቡድናችንን መልሰን አንስተን ለዚህ ጨዋታ ባዘጋጀንበት መንገድ እና በነበረን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይህንን ማሳካታችን በጣም ያኮራል” ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም ቡድናቸው ላለፉት 14 ዓመታት ሊያሳካ ያልቻለውን ታሪካዊ ተልዕኮ ማሳካቱን ገልጸው፣”ይህ ላለፉት 14 ዓመታት ሳናሳካው የቀረ ትልቅ ተልዕኮ ነበር። በአንፊልድ ለማሸነፍ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ እና በተሟላ ሁኔታ መተግበር እንዳለብን፣ እንዲሁም ሊቨርፑል የሚፈጥራቸውን የፈተና እና የማጥቃት ጫናዎችን ተቋቁመን ማለፍ እንዳለብን እናውቅ ነበር። የቡድኔ እንቅስቃሴ በጣም የሚያስደምም ነበር፤ ውጤቱም እጅግ አስደስቶኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
አርሰናል በአንፊልድ የነበረውን የሽንፈት ታሪክ ስለመቀየሩ የተጠየቁት አርቴታ”አሁን ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ውስጣዊ ስሜት ነበረኝ። በጨዋታው ወቅት በጥብቅ መከላከል፣ ውስን ግብ የማስቆጠር እድል ማግኘት እና በወሳኝ አጋጣሚዎች ላይ ደግሞ የነበረንን ብቃትና ጥራት አውጥተን መጠቀም ችለናል፤ በመጨረሻም ድሉን የእኛ አድርገናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
አርሰናል ይህንን ድል የተቀዳጀው በሳምንቱ በፍሊትዉድ ታውን ከገጠመው ያልተጠበቀ ሽንፈት በኋላ ቡድኑን እንደገና በማደራጀት በመሆኑ፣ ድሉ ለቀጣይ የዋንጫ ፉክክር ትልቅ የስነ-ልቦና ጥንካሬ እንደሚሰጠው ተገምቷል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ወላይታ ድቻ ወልዋሎን በማሸነፍ ተከታታይ ድል አስመዘገበ
ሀዋሳ ከተማ ጋሞ ጬንቻን በማሸነፍ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ድሉን አሳካ
የኤዝሪ ኮንሳ እና ጋብሬል ማጋሌሽ ድንቅ ጥምረት በአርሰናል