ሀዋሳ ከተማ ጋሞ ጬንቻን በማሸነፍ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ድሉን አሳካ

ሀዋሳ ከተማ ጋሞ ጬንቻን በማሸነፍ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ድሉን አሳካ

በ5ኛ ሳምንት ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ጋሞ ጬንቻን ከመመራት ተነስቶ 2ለ1 በማሸነፍ በዚህ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል።

ቀን 9 ሰዓት ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ለሀዋሳ ከተማ ሁለቱንም የማሸነፊያ ግቦች ቃልኪዳን ዘላለም አስገኝቷል።

ጋሞ ጬንቻን ምንም እንኳን ከሽንፈት መታደግ ያልቻለች ብትሆንም በሊጉ ታሪክ የመጀመሪያቸው የሆነችውን ጎል የትምጌታ ታደሰ አስቆጥሯል።

በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ሀዋሳ ከተማ ከ4 ጨዋታዎች በኋላ ነው የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው።

በአሰልጣኝ ማቲዎስ ለማ የሚመራው ጋሞ ጬንቻ በዚህ ዓመት 3ኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።

የዓመቱን የመጀመሪያውን ድል ያስመዘገበው ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 5 በማድረስ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው 10ኛ ደረጃን ይዟል።

እስካሁን ምንም ጨዋታ ያላሸነፈው ጋሞ ጬንቻ በተመሳሳይ አንድ ጨዋታ እየቀረው 1 ነጥብ ይዞ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሌላ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢላል ገመዳ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1ለ0 በማሸነፍ እንዲሁ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ የፕሪሚዬር ሊግ ድሉን አሳክቷል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ