የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማመንጨት በማባዛትና በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲሻሻል ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገለፀ
ይህ የተገለፀው በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ጉመርና አበሽጌ ወረዳዎች በማዕከሉ ድጋፍ በወጣቶችና በአርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ የገብስና የጤፍ ማሳ በባለድርሻ አካላት በተጎበኘበት ወቅት ነው።
በአለም 53 በኢትዮጵያ 43 እና በጉራጌ ዞን ደግሞ 51 በመቶ ማሳዎች በአሲዳማ አፈር መጠቃታቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪና ዋና ዳይሬክተር ቤተል ነክር በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማመንጨት በማባዛትና በማስተዋወቅ ለባለሙያዎችና ለአርሶአደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲሻሻል ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
የጉራጌ ዞን ግብርና ትልቁ ፈተና የአፈር አሲዳማንነት ነው ያሉት አቶ ቤተል፤ ይህን መነሻ በማድረግ ዘንድሮ በዞኑ በሶስት ወረዳዎች አርሶአደሮችና ወጣቶችን በማቀናጀት አሲዳማ ማሳዎችን በኖራ በማከም እንዲሁም ምርጥ ዘር በማቅረብ ምርትና ምርታማነት እንዲሻሻል ማስቻላቸውን አብራርተዋል።
አክለውም አሲዳማ አፈርን በኖራ ማከም በርካታ የሰው ኃይል እንዲሁም መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ የተቋማቸው አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የአፈር አሲዳማንነትን ተቋቁመው ምርት መስጠት የሚችሉ አማራጭ የሰብል ዝርያዎች ዘር ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ተቋሙ በዘርፉ በርካታ የምርምር ስራዎች እያከናወነ ሲሆን አገልግሎቱ በኦሮሚያና ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 4 ዞኖች እና 2 ልዩ ወረዳዎችን ተደራሽ በማድረግ በምርት ዘመኑ በጤፍ፣ በስንዴ፣ በገብስና በሽምብራ አዳዲስ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ ከ285 ሄክታር በላይ ማሳ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ምርምራቸው በአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑንና የማህበረሰብ አቀፍ የዘር ብዜት ማዕከላት የማጠናከር ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አሲዳማ መሬት በኖራ የማከም ምርጥ ዘር በወቅቱ የማቅረብን ተግባር ጨምሮ አርሶአደሩ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ እንዲያከናውን ክህሎቱ የማሳደግ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይልማ ሰይፈ እና የጉመር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደገሙ አለሙ በወረዳዎቹ የአፈር አሲዳማነት በስፋት እንደሚገኝ በመግለጽ ይህንን በመከላከል ምርት እና ምርታማነት ለማሻሻል የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች በመሆኑ በቅንጅት እየተሰራ የሚገኘው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ከተቋሙ የተደረገለት የግንዛቤ እና ሌሎች ድጋፎች ወደ ተግባር በመቀየር ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምሁር አክሊል እና ጉመር ወረዳዎች ተደራጅተው የስንዴና የገብስ ኩታ ገጠም እርሻ እያለሙ የሚገኙ ወጣቶችና እርሶ አደሮች የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ማሳቸውን በኖራ በማከም ምርጥ ዘር በማቅረብ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረጉ አመሰግነው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በአርሶ አደር ቀን በዓል መርሃ ግብሩ ላይ ከፌደራል ከቢሾፍቱና ሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከላት ከጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያና ከሶስቱም ወረዳዎች የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣያችን

More Stories
ብቁ፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ ትውልድ ለማፍራት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ
ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በቅንነት እና በታማኝነት መፈጸም እንዳለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ አሳሰቡ
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር በህዝቦች መካከል አንድነትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያግዝ መሆኑ ተገለፀ