ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በቅንነት እና በታማኝነት መፈጸም እንዳለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ አሳሰቡ

ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በቅንነት እና በታማኝነት መፈጸም እንዳለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ አሳሰቡ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት እና የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ባለሙያዎች በየተቋማት ለመፈጸም በታቀዱ ተግባራት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋማት የክልሉ ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽንና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አመራሮች እና ባለሙያዎች የተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና የጋራ መግባባትን በመፍጠር በቀጣይ ውጤታማ ተግባራትን ለመፈጸም ያግዛል ተብሏል።

በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ፤ ሰባተኛው ጠቅላ ምርጫ ተካሂዶ የመደመር መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ አዳዲስ የአመራር ምደባ ተካሂዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸው ሕዝቡ የሰጠንን ይሁንታ እንደ ዕድል በመጠቀም ከሕዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ መወጣት ይገባል ብለዋል።

አመራሩ እና ሲቪል ሰርቫንት በየተሠማራበት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመሥጠት የተገልጋይ እርካታ መጨመር እንዳለባቸው ዋና አፈ ጉባኤዋ መክረዋል።

የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት አዋጆችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ የክትትልና ቁጥጥር ስራ በአግባቡ ማከናወን እንዳለባቸው የመከሩት ዋና አፈ ጉባኤዋ፤ በመንግሥት የሚበጀተውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ከማዋል አኳያ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ዕንቁ ዮሐንስ ስልጠና በሰጡበት ወቅት፤ በየተቋማት ያሉ አመራሮች እና ፈጻሚ ባለሙያዎች የመፈጸም እና ማስፈጸም አቅማቸውን በማጎልበት የቁጥጥር እና ክትትል ሥራቸውን በቅንነት እንዲተገብሩ አሳስበዋል።

የመንግሥት ሠራተኛው ተግባራትን በቡድን መንፈስ በቅንነት እና በታማኝነት በመከወን ለውጤት መትጋት እንዳለባቸውም አቶ ዕንቁ ገልጸው የሥራ ተነሳሽነትን በመጨመር ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ተግባራትን በአግባቡ መከወን እንዳለባቸው ተብራርቷል።

በስልጠና መድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ዋና እና ምክትል አፈ ጉባኤ፣ ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን