ብቁ፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ ትውልድ ለማፍራት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ የእዣ ወረዳ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሸምሱ አክመል ገለፁ።
የጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት “የትምህርት ጥራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል አመታዊ ጉባኤውን አካሄዷል።
የእዣ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሸምሱ አክመል በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለትምህርት ጥራት ውጤታማነት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል።
የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ በማድረግና ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ሁሉ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው መከታተል እንዲችል በትኩረት ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።
ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሁም ውጤታማ ትውልድ ለማፍራት ከመሰረቱ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያሻም አመላክተዋል።
ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በማስፋት የትምህርት ግብዓት ለማሟላት የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አቶ ሸምሱ ተናግረዋል።
የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንደገለፁት፤ ትምህርት የሁሉም ልማትና እድገት መሠረት ነው።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ79 ሚሊየን 916 ሺህ 825 ብር በላይ ብር ከትምህርት ባለድርሻ አካላት በማሰባሰብ 35 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች በመገንባትና የትምህርት ቁሳቁሶች በማሟላት ትምህርት ቤቶች ለመማሪያ ምቹ እንዲሆኑ ተሰርቷል ብለዋል።
ለትምህርት ጥራት መምጣት የመምህራን ሙያዊ ክህሎት ማሳደግ ተማሪዎች ትምህርት በአግባቡ እንዲከታተሉ ማድረግ የትምህርት ተቋማት ግብዓት መሟላት ወሳኝ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የእዣ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ፅሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አስቻለው ወልዴ በበኩላቸው፤ የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚረጋገጠው ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ማድረስ ሲቻል ነው ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች ጊዜ ከሚሻሙ ድርጊቶች በመታቀብ ትኩረታቸውን ትምህት ላይ እንዲያድርጉ መምህራን እና ወላጆች የበኩላቸውን መወጣት ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በክልላዊና ሀገራዊ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ተቋማት እውቅና ተሠጥቷል።
ዘጋቢ፡ አማረ መንገሻ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በቅንነት እና በታማኝነት መፈጸም እንዳለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ አሳሰቡ
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር በህዝቦች መካከል አንድነትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያግዝ መሆኑ ተገለፀ
በጎፋ ዞን በተያዘው የምርት አመት ከ5 ሺህ 211 በላይ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።