ዓለምን ያስደመሙት የ90 ዓመቱ ጃፓናዊ የአካል ብቃት ተወዳዳሪ

ዓለምን ያስደመሙት የ90 ዓመቱ ጃፓናዊ የአካል ብቃት ተወዳዳሪ

በስፖርት ዓለም ዕድሜ መሰናክል አለመሆኑን በተግባር ያረጋገጡት አዛውንቱ ጃፓናዊ አትሌት ቶሺሱኬ ካናዛዋ፣ በ90 ዓመታቸው በስፔኗ ሳንታ ሱሳና ከተማ በተካሄደው የ2026 IFBB ዓለም አቀፍ የአካል ብቃት እና የሰውነት መገንባት ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል።

እ.ኤ.አ በነሐሴ 1936 የተወለዱት ካናዛዋ፣ በስፔኑ መድረክ ላይ ከእሳቸው በአሥር ዓመታት ከሚያንሱ ወጣትና ጎልማሳ ተወዳዳሪዎች ጎን ለጎን በመሰለፍ ያሳዩት ድንቅ የአካል ብቃት፣ ጽናትና ውበት የታደሙትን ተመልካቾችና የውድድሩን ዳኞች በከፍተኛ ሁኔታ አስገርሟል።

ቶሺሱኬ ካናዛዋ የአካል ብቃት ስፖርትን የጀመሩት በ20 ዓመታቸው አካባቢ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1960 እና በ1963 የጃፓን ሚስተር ጃፓን ክብርን መጎናፀፍ ችለዋል።

እ.ኤ.አ. በ1967 በካናዳ በተካሄደው የሚስተር ዩኒቨርስ ውድድር ከታዋቂው አርኖልድ ሺዋርዜነገር ጋር በመወዳደር 4ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀው ነበር።

በ34 ዓመታቸው ከውድድር ራሳቸውን አግልለው የነበሩት ካናዛዋ፣ በ50 ዓመታቸው የታመሙ ባለቤታቸውን ለማበረታታትና “ማንኛውም ነገር ይቻላል” የሚል ተስፋ ለመስጠት እንደገና ወደ ብረት ማንሳት ልምምድ ተመልሰዋል።

 ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ልምምዳቸውን ሳያቋርጡ በከፍተኛ ዲሲፕሊን በመቀጠል በቅርቡ በጃፓን በተካሄደው የዕድሜ ባለፀጐች  ውድድር ላይ ከ85 ዓመት በላይ የውድድር ዘርፍ ላይ አሸናፊ በመሆን 19ኛ የሀገራቸውን ሻምፒዮንነት ዋንጫ አንስተዋል።

ቶሺሱኬ ካናዛዋ ስለ ረጅም ዕድሜና ጤናማ የአካል ብቃት ምስጢራቸው ሲናገሩ “ተፈጥሮአዊ ምግቦችን አዘውትሮ መጠቀም፣ ከአልኮልና ከሲጋራ መራቅ፣ እንዲሁም ዕድሜ ቢገፋም በቀን ውስጥ የሚቻልን ያህል እንቅስቃሴ ማድረግ ለውጤት ያበቃል” ብለዋል።

ይህ በ90 ዓመታቸው በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ያሳዩት ተሳትፎ ጽናትና ህልም በዕድሜ አይወሰኑም የሚል ትልቅ አስተምህሮ ለዓለም  ህዝብ አስተላልፏል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ