ካርሎስ ቴቬዝ ከማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ማንቼስተር ሲቲ ያደረገው ዝውውር በበቀል ላይ የተመሰረተ እንደነበር ተናገረ

ካርሎስ ቴቬዝ ከማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ማንቼስተር ሲቲ ያደረገው ዝውውር በበቀል ላይ የተመሰረተ እንደነበር ተናገረ

አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ካርሎስ ቴቬዝ በተጫዋችነት ዘመኑ ከዓመታት በፊት ከማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ተቀናቃኙ ማንቼስተር ሲቲ ያደረገው ዝውውር እውነተኛው ምክንያት በቀል ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ተናግሯል።

ተጫዋቹ በማንቸስተር ዩናይትድ ከቀድሞ የቡድን አጋሩ ሪዮ ፈርዲናንድ በነበረው ቆይታ እንደገለጸው፣ በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን የገቡትን ቃል ባለማክበራቸው ከፍተኛ ውንጀላ ተሰንዝሮባቸዋል።

እንደ ቴቬዝ ገለጻ፣ ፈርጉሰን ከሁለት ዓመት የውሰት ውል በኋላ የቋሚ ዝውውር ውሉን እንደሚፈጽሙለት ቃል ገብተውለት ነበር።

“ፈርጉሰን ‘ካርሎስ፣ የዝውውር ክፍያህን ፈጽሜ በማንቼስተር እንድትቆይ አደርጋለሁ” ብለውኝ ነበር የሚለው ቴቬዝ “በርባቶቭን ለማስፈረም ገንዘብ እንደሚወጣ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ለአንተም የሚፈለገውን ክፍያ ፈጽመን ውል እናስፈርምሃለን ብለው ቃል ገብተውልኝ ነበር” ሲል ቴቬዝ አስታውሷል።

ነገር ግን ፈርጉሰን የሰጡትን ቃል ሳይጠብቁ ቀርተዋል። ይባስ ብሎም የቴቬዝን የገበያ ዋጋ ለማውረድ ሲሉ ተጫዋቹን በተደጋጋሚ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ማስቀመጥ እንደጀመሩ ተናግሯል።

“በእኔ እይታ፣ የእኔን የዝውውር ዋጋ ለማውረድ ሲል ወደ ጎን ሊገፉኝ ጀመር” ሲል የተናገረው ቴቬዝ “ይሄ ደግሞ በጣም አሳዝኖኛል፤ ልቤንም ሰብሮታል። ላደረግሁት ነገር ሁሉ የሚገባኝን ምላሽ አላገኘሁም። ስለዚህ ወደ ማንቼስተር ሲቲ ያደረግሁት ዝውውር ለእኔ የ‘በቀል’ ያህል ነበር” ሲል አርጀንቲናዊው አጥቂ ይፋ አድርጓል።

በወቅቱ የኦልድ ትራፎርድ ደጋፊዎች ፈርጉሰን ተጫዋቹን በቋሚነት እንዲያስፈርሙት በስታዲየም ውስጥ ፈርጊ፣ አስፈርመው! እያሉ ይጮሁ እንደነበር ይታወሳል።

ቴቬዝም የዩናይትድ ደጋፊዎች ላሳዩት ፍቅር ትልቅ አክብሮት እንዳለውና ሁኔታውን እንደሚረዱት ገልጿል።

ካርሎስ ቴቬዝ በዩናይትድ በነበረው የሁለት ዓመት ቆይታ በ99 ጨዋታዎች 34 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፣ የቻምፒዮንስ ሊግ እና የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።

በመቀጠልም በወቅቱ በብሪታንያ የዝውውር ታሪክ ከፍተኛ በሆነ በ47 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ማንቼስተር ሲቲ በመቀላቀል በ148 ጨዋታዎች 73 ጎሎችን በማስቆጠር የሲቲ የስኬት ዘመን መነሻ አካል መሆን ችሏል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ