ባየር ሙኒክ ለባሎንዶር አሸናፊው ሃሪ ኬን የጀግና አቀባበል አደረገ

ባየር ሙኒክ ለባሎንዶር አሸናፊው ሃሪ ኬን የጀግና አቀባበል አደረገ

የጀርመኑ ሀያል ክለብ ባየር ሙኒክ፣ የ2026 የዓለማችን ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች በመባል የባሎንዶር ክብርን የተቀናጀውን እንግሊዛዊ አጥቂ ሃሪ ኬንን ወደ አሊያንዝ አሬና ስታዲየም ሲመለስ የጀግና አቀባበል አድርጎለታል፡፡

ባለፈው ሰኞ ምሽት በለንደን በተካሄደው የሽልማት የስነ-ስርዓት የዓለማችንን ከፍተኛ የግል እግር ኳስ ክብር ባሎንዶርን ማሸነፉን ተከተሎ፣ ሃሪ ኬን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ክለቡ ስታዲየም አሊያንዝ አሬና ሲመለስ በቡድን አጋሮቹ እና በአሰልጣኞች ልዩ አቀባበል ተደርጎለታል።

ባየር ሙኒክ ትናንት ምሽት በጀርመን ካፕ ከማግዴበርግ ጋር ካደረገው ጨዋታ አስቀድሞ፣ የክለቡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች በሁለት ረድፍ በመሰለፍ ለ33 ዓመቱ እንግሊዛዊ አጥቂ የክብር ሰልፍ በመስራት ሞቅ ባለ ጭብጨባ አቀባበል አድርገውለታል።

ከዚህ በተጨማሪም ታዋቂው የአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ውጫዊ ገጽታ የስኬቱን ታላቅነት በሚገልጽ ወርቃማ ቀለም እና በሃሪ ኬን ስም በደመቀ መብራት አብርቶ ታይቷል።

ሃሪ ኬን ባለፈው የውድድር ዘመን ያስመዘገበው አስደናቂ የግብ እና የግብ እድል የመፍጠር ቁጥር ለዚህ ታሪካዊ ሽልማት ያበቃው ሲሆን፣ በባየር ሙኒክ ታሪክ ከጀርመኖቹ የእግር ኳስ ዝነኞች ገርድ ሙለር፣ ፍራንዝ ቤከንባወር እና ካርል-ሃይንዝ ሩመኒገ በመቀጠል 4ኛው የባሎንዶር አሸናፊ ተጫዋች መሆን ችሏል።

በተጨማሪም ለባየር ሙኒክ ይህንን ዋንጫ ያሸነፈ የመጀመሪያው የውጭ ሀገር ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።

ሃሪ ኬን ለተደረገለት ደማቅ አቀባበል ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን “ይህንን ታላቅ ሽልማት ወደ አሊያንዝ አሬና በማምጣቴ ትልቅ ክብር ይሰማኛል፤ ለዚህ ስኬት የበቃሁት በቡድን አጋሮቼ፣ በአሰልጣኞቼ እና በደጋፊዎቻችን ሙሉ ድጋፍ ነው” ሲል ተናግሯል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ