በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጤናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የወላይታ ዞን አስተዳደር ገለጸ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጤናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የወላይታ ዞን አስተዳደር ገለጸ

የዞኑ ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር የጤና አገልግሎት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነት እና ጥራት አኳያ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

የህዝቡን ማህበራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ በአትኩሮት ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት ደረጃ ለማሻሻል በተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

በዚህም ጠበላ እና ባለ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን ጀነራል ሆስፒታል ደረጃ የማሻሻል ሥራ መሰራቱን ጠቁመው፥ ህዝቡ በቅርበት የፈውስ ህክምና እንዲያገኙ መደረጉንም አስረድተዋል።

በቀጣይም ደረጃውን የጠበቁ ሆስፒታሎችን በማደራጀትና እና የላቦራቶሪ ማዕከላትን በመገንባት ጥራት ያለው ህክምና ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የወባ በሽታን ቀድሞ የመከላከል ተግባር በተሰጠው ትኩረት ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮ ዓመት 50 ከመቶ የወባ ሥርጭት መቀነስ መቻሉን አክለዋል።

በዞኑ አንዳንድ የጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በተደረገው ጠንካራ ትግል 18 የህዝብ መድኀኒት ፋርማሲዎች ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አመላክተዋል።

በቀጣይም ከተደራሽነት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት በዞኑ በርካታ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ የጤና ተቋማት ግንባታ የማስጀመር ሥራ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ አክለዋል።

የእናቶች እና ህፃናት ሞት ለመቀነስ ሰፊ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን አንስተው፥ በተለይም ከአንቡላንስ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል።

በበጀት አመቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክረው በማስቀጠል የታዩ ክፍተቶችን በማረም በሙሉ አቅም እንሰራለን ሲሉ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

የጤና ባለሙያዎች ተጨማሪ ሰዓት ክፍያና ከባለሙያዎች የሚነሳውን ቅሬታ በ2019 በጀት ዓመት ትኩረት የምንስጥባቸው ዘርፎች አንዱና ዋንኛው ነው ሲሉ አክለዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ በበኩላቸው 2018 በጀት ዓመት በሁሉም የጤና ልማት ስራዎች የዞኑን ህዝብ ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለበት ዓመት እንደነበር ጠቁመው፥ የጤና ተቋማት ተደራሽነት፣ የህክምና ግብአት አቅርቦት እና ብቁ የሰው ሀይል ከማደራጀት አኳያ ባለፉት ግዚያት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸዉ ብለዋል።

የእናቶች እና የህፃናት ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ለጤና ባለሙያዎች ተገቢ ስልጠናዎችን ከመስጠት አኳያም ሰፊ ስራዎች እየተሰራ መቆየቱን አክለዋል ።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ተሞክሮዎችን በማስፋት በተለይም ጉድለት የታየባቸው ጉዳዮች ላይ በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን