በክልሉ የሚገኙ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የአሰራር ማነቆዎችን መፍታት ያስፈልጋል – ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር)
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ የመደመር መንግስት ምስረታን ተከትሎ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2019 ዕቅድ ዙሪያ የፈፃሚ ማዘጋጃ መድረክ በአርባምንጭ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ የመደመር መንግስት ከተመሰረተ በኋላ በክልሉ የሚገኙ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አውስተው፤ የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት ስኬቶቻችንን ለመለካት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ የሁሉም የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ 79 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚኖርበትን የገጠር አከባቢን በግብርናው ዘርፍ ትራንስፎርም ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብርናን ማዘመን እና ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ እንደሚያሻ አብራርተው፤ በምርቶቻችን ላይ እሴቶችን በመጨመር ዘርፉ የስራ እድል እንዲፈጥር ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) የቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ዘርፎችን በማጠናከር ኢኮኖሚውን ማነቃቃትና ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር እመርታን ለማስመዝገብ በክህሎት ልማት፣ በገበያ ትስስር፣ ግብዓት አቅርቦት እና መሰል ማነቆዎችን በጋራ መፍታት ይጠበቅብናል ሲሉ አመላክተዋል።
በመርሀ -ግብሩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር)፤ በ2018 በጀት ዓመት በግብርና፣ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች የተሻለ ስራ መሰራቱን ገልፀው፤ በቀጣይም በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ከአቅርቦት ተኮር ስልጠና ወደ ፍላጎት ተኮር ስልጠና ማሸጋገር ያሻል ሲሉ ተናግረዋል።
ተቋሞቻችንን የፈጠራና የልህቀት ተቋም እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ያሻል ያሉት ደምሴ አድማሱ(ዶ/ር)፤ ከእነዚህ ተቋማት የሚወጡ አሰልጣኞች በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም አሳስበዋል።
የስራ፣ ስራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፤ ፀጋዎችን የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ወደ እውነተኛ ብልፅግና ለመቀየር ቅንጅታዊ አሰራርን ማስፈን ያስፈልጋል ብለዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ፈተናዎችን ወደ እድል የሚቀይሩ አሰራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፤ በቀጣይም የሚጠበቁ ድጋፎችን ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን በተያዘው የምርት አመት ከ5 ሺህ 211 በላይ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
ግብርናን በማሻገር የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ የኢኒሼቲቭ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) በተገኙበት የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ የመደመር መንግስት ምስረታን ተከትሎ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 ዕቅድ ፈፃሚ ማዘጋጃ መድረክ በአርባምንጭ ተጀመረ