በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሰብላቸውን በህብረት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገለጹ

በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሰብላቸውን በህብረት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገለጹ

​የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ በመኸር ወቅት ከተዘራው ሰብል ከ480 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅና ለበጋ ወቅት ግብርና ስራዎችም አስፈላጊው የዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አስታውቋል።

​ወቅቱ አርሶ አደሮች የድካም ፍሬያቸውን የሚያጭዱበትና ምርታቸውን ወደ ጎተራቸው የሚያስገቡበት በመሆኑ የምርት ማሰባሰብ ስራ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።

​በሀዲያ ዞን አማካ ወረዳ ፎርቆሴ ቀበሌ ያነጋገርናቸው አቶ ተስፋዬ ሱሊቶ እና ወጣት ዳዊት አሽሶ የተባሉ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት፤ በመኸር ወቅት የዘሩትን የደረሱ ሰብሎች ማሰባሰብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

​አክለውም በአካባቢያቸው በብዛት የሚመረተውን ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመታደግ በህብረት በመሆን በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

​በፎርቆሴ ዊጤ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ሌላኛው አርሶ አደር ጌታቸው ብርሲዶ በበኩላቸው፤ ከሌሎች የሰብል ዓይነቶች በተጨማሪ የስንዴ ምርት በስፋት ማምረታቸውን ገልፀው፣ አሁን ላይ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የደረሱ ሰብሎች ያለ ምርት ብክነት በአግባቡ እንዲሰበሰብ በዘመናዊ ሜካናይዜሽን (ኮምባይነር) ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

​በሀዲያ ዞን የአመካ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጋደና በበኩላቸው፤ በመኸር ወቅት መጀመሪያ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን ጠቁመው፣ በዚህም የምርት መቀነስ እንዳያጋጥም በባለሙያዎች ሰፊ የክትትል ስራ ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል።

​በወረዳው በመኸር ወቅት የተወሰነ የብክነት መጠንን ታሳቢ በማድረግ የግብርና መሬት በልዩ ልዩ ሰብሎች መሸፈናቸውን ገልፀው፤ በዓመቱ 480 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።

የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ እንዲድኑ እና የምርት ብክነት እንዳያጋጥም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ወደ ስራ መገባቱንም ጠቁመዋል።

​ከመኸር ስራ በመቀጠል በአካባቢው ያሉ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ ልማት ስራ የተለያዩ ሰብሎችንና የጓሮ አትክልቶችን ለማምረት ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊው አስታውቀዋል።

​ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን