በጎፋ ዞን በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ልማቶችና በሌሎችም የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ልማቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ
በርዕሰ መሥተዳድሩ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ልዑክ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በመገኘት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው፤ የጎፋ ዞን ለግብርናው እድገት በሚጠቅሙ የተፈጥሮ ሀብቶችና በቱሪዝም ሀብቶች የታደለ አካባቢ መሆኑን ጠቁመው ያሉትን የልማት ዕድሎች በመጠቀም የአካባቢውን ብልጽግና ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የመስኖ አማራጮችን ማስፋፋትና የግብርና መካናይዜሽንን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህም የምርትና የምርታማነት ዕድገትን ከማረጋገጥ ባሻገር፣ አርሶ አደሩ ለደከመበት ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ የገበያ ትስስርን ማጠናከር የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ ያለውን የሌማት ትሩፋት ማስፋፋትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ የልማት አማራጮችን ማጠናከር ከትኩረት አቅጣጫዎች መካከል እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በትምህርት ዘርፍም የትምህርት ጥራትን ማሳደግና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማስቻል የልማት ሥራዎች አንዱ ቁልፍ አቅጣጫ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በመምህራን ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
በከተሞች ልማት ዘርፍ ከሚተገበሩ የ100 ቀናት ዕቅድ ተግባራት መካከል ከተሞችን ንጹህና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ እንዲሁም የመንግሥት ገቢን በአግባቡና ሙሉ በሙሉ መሰብሰብ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በተለይም በከተሞች የሚካሄደው የገቢ አሰባሰብ ሂደት ከሙስናና ከብልሹ አሠራር የጸዳ እንዲሆን አስፈላጊው ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
በሳውላና በሌሎችም ተጀምረው የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ከተሞችን ለኢንቨስትመንት ሳቢ፣ ለንግድና ለቱሪዝም ምቹ የሆኑ የግብይትና የቱሪዝም ማዕከላት ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስና የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም አካባቢው ሰላማዊ፣ የተረጋጋና ለልማት ምቹ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ አመራሩም የሕዝቡን ተሳትፎ በመደገፍ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ በመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሰኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አሰታወቀ
ሳውላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተካሄደ ነው
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማትና ሰላምን በማጽናት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል