በጎፋ ዞን በተያዘው የምርት አመት ከ5 ሺህ 211 በላይ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በጎፋ ዞን በተያዘው የምርት አመት ከ5 ሺህ 211 በላይ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው ዞናዊ የላሞችና ጊደሮችን በሆርሞን ማድራትና ማዳቀል የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ በዛንጋ ማዕከል አዋንዴ ቀበሌ አስጀምሯል።

በጎፋ ዞን ከ2 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ ከብቶች እንደሚገኙ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፤ ነገር ግን የብዛታቸውን ያክል ምርት እንዲሰጡ ለማስቻል ዝርያቸውን የማሻሻል ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ እንደተናገሩት፤ ከመደበኛው ጎን ለጎን ላሞችና ጊደሮችን በሆርሞን ማድራትና ማዳቀል የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ ከ5 ሺህ 211 በላይ ከብቶችን ለማዳቀል ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

የተጀመረው ዘመቻ በሁሉም ወረዳዎች በይፋ የተጀመረ በመሆኑ ሁሉም ከብት አርቢ አርሶ አደሮች በተቀመጡ ቀናት ከብቶቻቸውን ወደ ማዕከላት በማምጣት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከተማ ከበደ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት በያዘው ኢኒሼቲቭ መሠረት በወተትና በሥጋ መንደር በማደራጀት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማዳቀል የሚያገኘው ውጤት እየጨመረ በመምጣቱ ከምግብ ዋስትና በዘለለ የገቢ ምንጭን ማስፋት ተችሏል ብለዋል።

የደንባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብድቄ አዶላ በበኩላቸው፤ የወረዳው ቀበሌያት በአብዛኛው በድለባ፣ በወተትና አይብ ምርት የሚታወቁ ቢሆንም በዘመናዊ አረባብ ሂደት ከማዘመን አኳያ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን አመላክተዋል።

የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ሥራው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተሻሻለ የእንስሳት መኖ  ልማት ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በድቀላ መርሐ ግብሩ ከብቶቻቸውን ይዘው ከመጡ የአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ጣሰው ጻቃራ እና አርሶ አደር ባይራቴ በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ ላሞችንና ጊደሮችን በተሻሻለ ዝርያ ማዳቀል ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚነታቸው መጨመሩን ተናግረው፤ ከብቶቹ ለሆርሞኑ ምላሽ በሚሰጡበት ወቅት አዳቃይ ባለሙያዎች በወቅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ቅርንጫፍ ጣቢያችን