በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 4 ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይባቸው አራት ትልልቅ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል በኤምሬትስ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ የሚደረገው የአርሰናል እና ኤቨርተን ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ካደረጋቸው ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ስድስቱን አሸንፎ በድል ጎዳና ላይ የሚገኘው አርሰናል፣ ዛሬም አሸንፎ ጉዞውን መቀጠል ይፈልጋል።
ይሁን እንጂ ባሳምንቱ አጋማሽ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከባየር ሙኒክ ጋር ከባድ ጨዋታ አድርጎ አቻ መለያየቱ ይታወሳል።
በስድስት ቀናት ውስጥ ሦስተኛ ጨዋታውን የሚያደርገው አርሰናል፤ ባለፈው ሳምንት በቼልሲ 2ለ0 የተሸነፈውን ኤቨርተንን ይገጥማል።
በአሰልጣኝ ዴቪድ ሞይስ የሚመራው ኤቨርተን በ10 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወደ ሰሜን ለንደን በማቅናት ከመድፈኞቹ ጋር ይፋለማል።
አርሰናል በዛሬው ጨዋታ ቡካዮ ሳካን፣ ክሪስቶስ ዞሊስን እና ዊሊያም ሳሊባን በጉዳት ምክንያት አያገኝም።
የዕለቱ ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ በስታምፎርድ ብሪጅ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ቼልሲ ከቶትንሃም የሚገናኙበት የለንደን ደርቢ ነው።
ባለፈው ሳምንት ኮቬንትሪን በማሸነፍ የመጀመሪያ የሊግ ድሉን ያስመዘገበው ቶተንሀም ሆትስፐር፣ ተከታታይ ድል ለማግኘት ከሜዳው ውጪ ከሰማያዊዎቹ (ቼልሲ) ጋር ይፋጠጣል።
በአሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ የሚመራው ቼልሲ ከሀገራት የጨዋታ ሰሞን በኋላ ያከናወናቸውን ሁለቱንም የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በማሸነፍ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛል።
በቼልሲ በኩል ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ እና ሬስ ጄምስ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል።
በቶትንሃም በኩልም እንዲሁ ዣቪ ሲሞን፣ ሉካስ ቤርግቫል፣ ዴስትኒ ኡዶጊ እና ሳቪኒሆ በጉዳት፤ ሮድሪጎ ቤንታንኩር ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም።
ከሁለቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ሌላኛው አጓጊ ጨዋታ አስቶንቪላን ከ ማንችስተር ሲቲ ቀን 8 ሰዓት 30 በቪላ ፓርክ ያገናኛል።
የሊጉ መሪ ማንችስተር ሲቲ አሸናፊነቱን ይዞ ለመቀጠል ወደ በቪላ ፓርክ ከባድ ትንቅንቅ ይጠብቀዋል።
እስካሁን ያደረጋቸውን ሁሉንም የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ፣ በዛሬው ዕለትም አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ጠንካራ ፍልሚያ ያደርጋል።
በሲቲ በኩል በሳምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እረፍት የተሰጠው ግዙፉ አጥቂ ኤርሊንግ ሀላንድ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።
አንቱዋን ሴሜኒዮ ግን ከዛሬው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል።
በአስቶንቪላ በኩል ደግሞ አማዱ ኦናና እና አሮን ዋን ቢሳካ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።
ኮቬንትሪ ሲቲ ከፉልሃም ከቀኑ 11 ሰዓት የሚገናኙበት ዛሬ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ!
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የ10 ጨዋታዎች ቅጣት ተላለፈባቸው
የብሩኖ ፈርናንዴስ መኖሪያ ቤት ተዘረፈ