‎ግብርናን በማሻገር የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ የኢኒሼቲቭ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ

‎ግብርናን በማሻገር የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ የኢኒሼቲቭ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ

‎

‎ግብርናን በማሻገር የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ የኢኒሼቲቭ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ኢትዮጵያዊ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

‎

‎በክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ካርታ ካስኬ የተመራ ልዑክ በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎች እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

‎

‎የክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም FSRP እያከናወነ የሚገኘው የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት እድሳት ሥራዎች እና የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንቅስቃሴዎችን የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የመስክ ምልከታ ካደረጉባቸው ሥፍራዎች የሚጠቀሱ ናቸው።

‎

‎በጉብኝቱ ወቅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ካርታ ካስኬ፤ ባዩት ለውጥ መደሰታቸውን ገልፀው፤ ኢትዮጵያ ግብርናን በማሻገር የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል የጀመረችው ጥረት መሬት ወርዶ እየተተገበረ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

‎

‎ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ብሎም የአርሶአደሩን ህይወት ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ አኳያ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ ያሉት ዶ/ር ካርታ፤ የክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም FSRP በዚህ ረገድ የሚበረታታና አዎንታዊ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

‎

‎ይህን የእውቀት ሽግግር በመጠቀም አርሶአደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ወደ መስኖ ልማት ሥራዎች ፊቱን በማዞር ይበልጥ ምርታማነቱን ለማሳደግ ሊተጋ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

‎

‎የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሩፎ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም FSRP እየተጫወተ ስላለው የማይተካ ሚና አመስግነዋል።

‎

‎በየአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ተዘዋውረው የተመለከቱትን አመርቂ ውጤት በእያንዳንዱ አርሶአደር ማሳ ለመተግበር የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

‎

‎የቡሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መኩሪያ በበኩላቸው፤ አከባቢው በምቹ የአየር ጸባይና የውሃ ሀብት የታደለ እና በዞኑ በምርታማነታቸው ከሚጠቀሱ ወረዳዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአፈር አሲዳማነት ችግር የግብርናው ዘርፍ ትልቁ ማነቆ በመሆኑ ክልሉ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

‎

‎አያይዘውም በወረዳው ህገወጥ የእንስሳት ግብይትን ለመከላከል በFSRP ድጋፍ እየተገነባ ያለውና ግንባታው ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ እየተሸጋገረ የሚገኘው የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል በክልሉ፣ በዞኑ እና በወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል፡፡

በዕለቱ በወረዳው ኮቾሬ ቀበሌ በከፍተኛ ወጪ የተገነባው የአርሶአደር ማሰልጠኛ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

‎

‎ዘጋቢ፡ ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን