ጥራት ያለው መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ የባለሙያን አቅም ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሚዛን ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ትእዛዙ ኬንጫ ተናገሩ፡፡
ቅርንጫፍ ጣቢያው ለተቋሙ ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ ለተቋሙ ሠራተኞች የሙያ ክህሎትን ለማሳደግ፣ የሥራ አፈጻጸምን ለማሻሻልና የሚዲያ አገልግሎትን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠት ጀምሯል።
የተቋሙ ስራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ ኬንጫ እንዳሉት፤ የሚዲያ ተቋማት ለሕብረተሰቡ ትክክለኛ፣ ፈጣንና አስተማማኝ መረጃ በማቅረብ ረገድ የሚኖራቸውን ሚና በብቃት ለመወጣት የሠራተኞችን የሙያ አቅም ማጎልበት ወሳኝ ነው፡፡
በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚዛን ቅርንጫፍ የጀመረው የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሠራተኞችን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ የሥራ ጥራትን ለማሻሻል እንደሚረዳም ገልጸዋል።
ሥልጠናው በዜና አዘገጃጀት፣ በሚዲያ የሥራ ሂደት፣ በቴክኒክ አጠቃቀምና በሙያዊ ሥነ-ምግባር ዙሪያ የሠራተኞችን አቅም ለማጠናከር እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ የተቋሙ ሰራተኞች ያላቸውን ክህሎት እንዲያሳድጉ እና በስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል።
አያይዘውም ሰልጣኞች ተቋማዊ የአሰራር ስርዓትን እንዴት መረዳት እንዳለባቸው፣ የሚሰጣቸውን ተግባር እንዴት መፈፀም እንዳለባቸው እና እንደ ተቋም በስነ-ምግባር መታነፅ አስፈላጊ መሆኑን በሚዳስሱ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ስልጠና እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
የተቋሙ ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የይዘት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መኮንን ኢያርዝ በበኩላቸው፤ ስልጠናው በዋናነት የራስን አቅም መገንባት በመሆኑ ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች ለስልጠናው ትኩረት በመስጠት የሚያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ብቁ እና ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ስልጠናው የጋዜጠኞች ስነ-ምግባር፣ የዜና እና ፕሮግራም አፃፃፍ፣ የምስል አቀራረፅ ጨምሮ የዜና እና ፕሮግራም ኤዲቲንግ በተመለከተ በንድፈ ሃሳብና በተግባር በተደገፈ መልኩ እንደሚሰጥ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡ ተመስገን ዳጉሳ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
ለሥራ ምቹ የሆኑ ተቋማትን መገንባት ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል የኣሪ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
ድክመታችንን በማረምና ጠንካራ ጎናችንን በማስቀጠል በ2019 ዓ.ም ለሚዲያችን ውጤታማነት እንተጋለን- በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
የአርሰናሉ አርክቴክት አርሴን ቬንገር የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩበት ቀን