ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የንብ ቀፎዎች እና የቦንጋ በግ ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ

ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የንብ ቀፎዎች እና የቦንጋ በግ ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ

ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የንብ ቀፎዎች እና የቦንጋ በግ ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች መሰራጨታቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የሌማት ትሩፋት ሥራን ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ተጠቁሟል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በተገኙበት በዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም (SLMP) በክልሉ ከ6 ወረዳዎች ለተውጣጡ አርሶና አርብቶ አደሮች ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የንብ ማነቢያ ቁሳቁሶች፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች እና የቦንጋ በግ ዝርያዎች ድጋፍ ተደርጓል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በክልሉ በሚገኙ 6 ወረዳዎች እና 55 ንኡስ ተፋሰሶች ከ78 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት የአካባቢን ተፈጥሯዊ ይዞታ ከማስተካከል ባለፈ የህብረተሰቡን ኑሮ እያሻሻለ ይገኛል።

በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ጠቁመው፤ ከ3 ሺህ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች እና የንብ ማነቢያ ቁሳቁሶች ለተጠቃሚዎች መከፋፈሉን አመላክተዋል።

በሀገሪቱ እውቅና ያላቸው 132 የቦንጋ በግ ዝርያዎች በተፋሰሶቹ ውስጥ እንዲራቡ ስርጭት መደረጉን አቶ ማስረሻ አስታውሰው፤ በግብርና ቢሮ ስር ያሉ ሁሉም ፕሮጀክቶች የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ በመከተልና በማከናወን የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል ፋይዳቸው የላቀ ነው ብለዋል።

ባለድርሻ አካላትም የተሰራጩ ሀብቶች አርሶና አርብቶ አደሩን በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ የክትትልና ድጋፍ ሥራ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም “SLMP” ከዚህ ቀደም የሌማት ትሩፋት ስራን የሚያሳልጡ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ የተደረገውን ድጋፍ ለታለመለት አላማ ለማዋል በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ዘጋቢ: ትዕግቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን