ድክመታችንን በማረምና ጠንካራ ጎናችንን በማስቀጠል በ2019 ዓ.ም ለሚዲያችን ውጤታማነት እንተጋለን- በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት

ድክመታችንን በማረምና ጠንካራ ጎናችንን በማስቀጠል በ2019 ዓ.ም ለሚዲያችን ውጤታማነት እንተጋለን- በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
‎
‎ድክመታችንን በማረምና ጠንካራ ጎናችንን በማስቀጠል በ2019 ዓ.ም ለሚዲያችን ውጤታማነት እንተጋለን ሲል በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ገለጸ፡፡

ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የ2018 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀም እና የ2019 እቅድ እንዲሁም የ1ኛ ሩብ አመት አፈፃፀም እየገመገመ ይገኛል፡፡
‎
‎በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉጃ ጉሜ፤ አንጋፋው የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከ50 በላይ በሚሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋ የሬድዮ ስርጭት የሚያደርግ ስመጥር ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።

‎አክለውም የዚህ ቅርንጫፍ የሆነው አርባ ምንጭ ኤፍኤም 90.9 በዞኖች አማርኛን ጨምሮ በ9 ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቋንቋ ስርጭቱን የሚያካሂድ መሆኑን አስታውሰው፤ ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ከ6 ሺህ በላይ ዜናና ፕሮግራሞችን በጥራት አዘጋጅቶ ለአድማጭ ጆሮ ማድረሱን አስታውቀዋል።
‎
‎ከሬድዮ ስርጭቱ ባለፈ በዋናው ሬዲዮና ቴሌቪዥን ማዕከል 332 የቴሌቪዥን ዜናና ፕሮግራሞችን ለአድማጭ ተመልካች ተደራሽ መደረጉንም ተናግረዋል።
‎
‎ተቋሙ እቅዱን ለመፈፀም በርካታ ተግዳሮቶችን እንዳስተናገደ፣ ለአብነትም ከፍተኛ የመብራት መቆራረጥ፣ የበጀት እጥረት፣ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እርጅና፣ የተደራሽነት ጥያቄ አለመመለስ እና የመሳሰሉ በርካታ ችግሮችን ለእቅድ አፈፃፀሙ እንቅፋት እንደሆነባቸውም አቶ ጉጃ አስታውቀዋል።
‎
‎ድክመታችንን በማረም ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል በ2019 ለሚዲያችን ውጤታማነት ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን፣ ጉልበታችንን እና እውቀታችንን በመደመር ለሀገርና ለአካባቢ ልማትና ለላቀ ውጤታማነት ልንተጋ ይገባል ብለዋል።

በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ መሉጌታ በበኩላቸው፤ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የባለፈውን በጀት ዓመት በርካታ ውጣ ውረዶችን በመጋፈጥና ወደ ውጤት በመቀየር ማሳለፉን ተናግረዋል።
‎‎
‎የተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርት፣ የ2019 እቅድና የ1ኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት በልማት እቅድ ባለሙያው አቶ አወል አሊ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በከተማዋ የሚገኘውን የሜቄዶንያ የአረጋዊን ማዕከልን የጽ/ቤቱ አመራሮች እና ሰራተኞች ጎብኝተዋል።
‎
‎በመጨረሻም የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሰራተኞች ከጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ እጅ የማበረታቻ ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።
‎
‎ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን- ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን