የአርሰናሉ አርክቴክት አርሴን ቬንገር የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩበት ቀን

የአርሰናልን እንዲሁም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ታሪክ ሙሉ በሙሉ የለወጡት ፈረንሳዊው ታላቅ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በመድፈኞቹ ወንበር ላይ ተቀምጠው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉበት ዕለት ዛሬ በታሪክ ይወሳል።

እ.ኤ.አ. ጥቅምት 12 ቀን 1996፤ ከ28 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር አርሰናልን በኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያ ይፋዊ ጨዋታቸውን መሩ።

በወቅቱ በኢዉድ ፓርክ በተካሄደው የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ አርሰናል ብላክበርን ሮቨርስን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ቬንገር ጉዟቸውን በድል ጀመሩ።ሁለቱንም የማሸነፊያ ግቦች ያስቆጠረው አንጋፋው አጥቂ ኢያን ራይት ነበር።

ይህ ጨዋታ ለሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል አዲስና ድንቅ የታሪክ ዕጥፋት አጋጣሚ ሆኖ ተቆጠረ፡፡

ቬንገር ወደ እንግሊዝ እግር ኳስ ሲመጡ አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብና መገናኛ ብዙኃን “አርሴን ማን ነው?” በማለት በጥርጣሬ ቢቀበሏቸውም፣ እሳቸው ግን የእንግሊዝን እግር ኳስ የጨዋታ ስልት፣ የልምምድ ባህል፣ የተጫዋቾች አመጋገብ እና የዝውውር ስትራቴጂ ሙሉ በሙሉ በመቀየር ትልቅ አብዮት ፈጥረዋል።

ፈረንሳዊው አሰልጣኝ መድፈኞቹን ለ22 ዓመታት በማሰልጠን በአጠቃላይ 1,235 ጨዋታዎችን በዋና አሰልጣኝነት መርተዋል።

እ.ኤ.አ. በ2003/04 የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ሙሉ የውድድር ዘመን (38 ጨዋታዎች) ሳይሸነፍ ዋንጫ ያነሳ የመጀመሪያው እና ብቸኛው አሰልጣኝ በመሆን የማይደፈር ታሪክ አስመዝግበዋል።

ከክለቡ ጋር 3 የፕሪሚየር ሊግ እና 7 የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን በማንሳት በኤፍ ኤ ካፕ ታሪክ ከፍተኛውን ዋንጫ ያነሱ አሰልጣኝ መሆን ችለዋል።

የክለቡን የአመጋገብ ባህል፣ የተጫዋቾችን ምልመላ ስርዓት እና የዓለም አቀፍ ተጫዋቾች ዝውውር መዋቅር በማዘመን ለዘመናዊው እግርኳስ እድገት ትልቅ መሰረት ጥለዋል።

አርሰናል ከሃይበሪ ወደ ኤምሬትስ ስታዲየም በሚሸጋገርበት ወቅት የነበረውን የፋይናንስ ጫና በመቋቋም አርሰናልን በተከታታይ ለ20 ዓመታት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማሳትፍ ችለዋል።

እንደ ቲየሪ ኦንሪ፣ ፓትሪክ ቪዬራ፣ ዴኒስ ቤርካምፕ እና ሲስክ ፋብሬጋስ ያሉ ዓለም አቀፍ ኮከቦችን ያበቁት አርሴን ቬንገር፣ እ.ኤ.አ. በ2018 ከአርሰናል ጋር ሲለያዩ ያስመዘገቡት ስኬትና የተዉት ታሪካዊ አሻራ እስከ ዛሬ ድረስ በፕሪሚየር ሊጉ በጉልህ ይነሳል።

በወቅቱ የስማቸው መጠራት አዲስ ሆኖባቸው “አርሴን ማን ነው?” ተብለው የተጠየቁት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ፣ በስተመጨረሻም ስማቸውን ከአርሰናል እና ከእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ጋር በወርቃማ ቀለም አፅፈው ጡረታ ወጥተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ