ኢትዮጵያ እና ሰንደቅ ዓላማ ተነጣጥለው አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያ ከክፉ ቅኝ ግዛት በትር እንኳን ያመለጠችው ለሰንደቅ ዓላማዋ የተዋደቁ ጀግኖች ስለነበሯት ነው፡፡
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያወሱት ኢትዮጵያ የትኛውንም በውጭ ኃይሎች የተከፈተባትን ጦርነት ተሸንፋ አታውቅም፡፡ በተለይም ለጥቁር ሕዝቦች ጭምር ኩራት የሆነውን የዓድዋን ጦርነት በጀግኖች ልጆቿ መክታ በድል ወራሪውን ኃይል መሸኘቷ የዚሁ ማሳያ ነው፡፡
ከዚያን ጊዜ በኋላም በውጭ ወራሪዎች የተከፈተባትን ጦርነቶች ሁሉ በድል ደምድማለች፡፡ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ እና የካራማራ ድሎች ዛሬም ድረስ ታሪክ የማይዘነጋቸው ትልቅ የትውልድ አሻራዎች ናቸው፡፡
ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችው በአሸናፊነት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ በየትውልዱ ሁሉ ጀግኖች ልጆቿ ለሰንደቅ ዓላማዋ ክብር ተዋድቀዋል፡፡ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባዮች ሲታይ የጀግንነት ምልክት ስለመሆኑ የሚጠራጠር የለም፡፡ ቀድሞ የተሰራው የድል ጀብድ ሰንደቅ ዓላማዋ እንዲከበር አድርጓል፡፡
ይህ ጀብድ ዛሬም በአዲሱ የመደመር መንግስት በልማት ሥራዎች እየተደገመ ነው፡፡ ድህነትን ታሪክ የሚሰራ ትውልድ በመደመር መንግስት እየተፈጠረ ነው፡፡ ቀድሞ ሀገሪቷ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ያደረገው የተጋዳይነት ገድል አሁን ወደ ድህነት ተሻግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ትልቁ ጠላት ድህነት ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግስት ብልጽግና ላይ ትኩረት አድርጎ የድህነትን ገጽታ ለመሻር ቆርጦ የተነሳው፡፡
ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በግብርና፣ በኢንደስትሪ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም ዘርፎች የሚደረጉ ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ሀገሪቱን ለማበልጸግ ሁነኛ መሳሪያዎች ሆነዋል፡፡ መንግስትም በዚሁ እንቅስቃሴ በያዝነው አዲሱ ዓመት ቀጥሏል፡፡
ይሄ በጀግንነት የሚታወቀውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በብልጽግና ደግሞ የበለጠ ከፍ የሚያደርገው ነው፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ለሰንደቅ ዓላማዋ የሚዋደቁ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ትውልዶች አሏት፡፡ ይህ ትውልድ ከሰንደቅ ዓላማዋ ጋር የማትነጣጠለዋን ኢትዮጵያ ስሟን ዳግም በብልጽና ከፍ ያደርገዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ኢያሱ ታዴዎስ

More Stories
የዳውሮ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት 12ኛ አስቸኳይ ጉባኤ እየተካሄደ ነው
አቶ ይሁን አሰፋ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ
አቶ መብራቴ ወልደማርያ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን ተሾሙ