የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ያስገነባቸውን 100 መኖሪያ ቤቶችን ለኮንሶ ዞን ተፈናቃዮች በይፋ አስተላለፈ‎

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ያስገነባቸውን 100 መኖሪያ ቤቶችን ለኮንሶ ዞን ተፈናቃዮች በይፋ አስተላለፈ
‎
‎የመጠለያው መገንባት የዜጎችን ክብር የመለሰ፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የትብብር ምልክት መሆኑም ተጠቁሟል።
‎
‎በመርሀ-ግብሩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ፤ በግጭት ለተጎዱ ወገኖች የተገነባው መጠለያ የዜጎችን ክብር የመለሰ፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የትብብር ምልክት ነው ብለዋል።
‎
‎ይህ ፕሮጀክት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡት አቶ ገሌቦ፤ የመጠለያ ግንባታው ጥላቻን በፍቅር ከመቀየሩም በላይ ተስፋን የሚያለመልምና መሰረትን የሚጥል የሰበብአዊነት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
‎
‎የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አብደላ ከማል (ዶ/ር)፤ የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል ከ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር 100 ቤቶችን በመገንባት ለተፈናቃዮች ማስተላለፉን ገልጸዋል።
‎
‎ዩኒቨርስቲው በአካባቢው በንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ በጤናው እና በግብርናው ዘርፍ የማህበረሰቡን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ ከመገኘቱም ባሻገር የህግ አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።
‎
‎በኮንሶ ዞን በዞን ገላቦ ቀበሌ፣ ኦሽኮ ንዑስ የተገነባው መጠለያም የዩኒቨርሲቲው ህግ ትምህርት ቤት አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን አብራርተው፤ ጌርዳ ሔርክልን ፕሮጀክትን፣ ኦክስፖርድ ብሩክስ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች አካላትን ለስኬቱ አመስግነዋል።
‎
‎የተላለፉት ቤቶች በፀሐይ ሀይል የሚሠራ 3 ሺህ ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚያስችል ሶላር የተገጠመላቸው ሲሆን በዚህም የገሊስ ቀበሌን መብራት ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተክሉ ወጋየሁ( ዶ/ር) ናቸው።
‎
‎መጠለያ ከተበረከተላቸው አካላት መካከል አቶ ኩታሶ ኩታዬ እና ጉይታ ኩታታ፤ በግጭት ምክንያት በሸራ ይኖሩ እንደነበር ተናግረው አሁን በተገነባላቸው መጠለያ ተረጋግተው እንደሚኖሩ ጠቁመው ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
‎
‎በፕሮጀክቱ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ግለሰቦችና ተቋማት የምስጋናና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
‎
‎በመርሀ-ግብሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አብደላ ከማል (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ተክሉ ወጋየሁ(ዶ/ር)፣ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞና ጥሪ የተደረገላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል።
‎
‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን