የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሚቀጥሉት ጊዜያት በክልሉ ትኩረት በሚሹ ዋና ዋና የልማት እና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ዙሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ ተወያይተዋል።

በዚህም ውይይት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልና የጎደሉትን ለመሙላት የክልሉ መንግስት ከሕዝቡ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ከጋሞ ዞን በተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የተነሱ የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) አብራርተዋል።

የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ከምርት እስከ ግብይት ባለው ሂደት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት ለመሥራት መታቀዱን ጠቁመዋል።

አያይዘውም በተለይ ሕዝቡ ሰላምና አንድነቱን በመጠበቅ ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን እንዲያጠናክር ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በጋሞ ዞን ብሎም በአርባ ምንጭ ከተማ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ተግባራት በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ጠይቀዋል።

በክልሉ ያሉ ጠቃሚ ባህላዊ ዕሴቶችን አጠናክሮ በመቀጠል የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማጠናከር የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

አክለውም በጋሞ ዞን ብሎም በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ የተፈጥሮ ሐብቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን የክልሉ መንግሥት በትኩረት እንዲሠራም የውይይቱ ተሳታፊዎች አመላክተዋል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን