ሹመት የምንዝናናበት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፅናት እና ለማበልፀግ የምንሰራበት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ሹመት የምንዝናናበት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፅናት እና ለማበልፀግ የምንሰራበት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ መስከረም 28/2019 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሹመት የምንዝናናበት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፅናት እና ለማበልፀግ የምንሰራበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመደመር መንግሥት ካቢኔያቸውን ለምክር ቤቱ በእጩነት አቅርበው ምክር ቤቱ ውይይት ካደረገ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረጡ የካቢኔ አባል ሚኒስትሮች ከትምህርት ዝግጅታቸው ባሻገር የሥራ ልምድ፣ የመፈፀም አቅም፣ የመከታተል ብቃት እና ያላቸውን ሥነ ምግባር መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የካቢኔ አባላቱ በቀጣዩ አምስት ዓመታት በትጋት መሥራት የሚችሉ፣ የሕዝብን አደራ በመቀበል ለመወጣት የሚጥሩ እና ሕዝብ አብዝቶ የሚጠይቀውን አገልግሎት ለመሥጠት የተዘጋጁ መሆኑን በተደረገ ክትትል መፈተሹን አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሮቹ ሌብነትን የሚጠየፉ ከመሆን ባለፈ ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ እና ሕዝብን ማገልገል መታደል እና ፀጋ መሆኑን በመረዳት ሀገርን ወደታሰበው ከፍታ ለመውሰድ በጊዜ የለኝም መንፈስ የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የመደመር መንግሥት እስከ 2050 የሚዘልቅ ስትራቴጂ ዕቅድ በማቀድ እየሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ተሿሚ ሚኒስትሮቹ ይህንን ዕቅድ የተረዱ እና የተገነዘቡ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡

የቀረቡ የካቢኔ አባላት መረጣ ላይ የብሔር እና የጾታ ሥብጥርን ለመጠበቅ ጥረት መደረጉን ገልፀው፤ የካቢኔ አባላት መሾም ሸክም መሆኑን በሚገባ መረዳት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

ተሿሚዎች ሹመት የምንዝናናበት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፅናት፣ ለማበልፀግ እና ድምፅ የሰጠውን የ54 ሚሊየን ሕዝብ አደራ ለመወጣት ያለእንቅልፍ ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት መሆኑን መረዳት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ካሱ ብርሃኑ