ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው በሙሉ ድምጽ ጸድቋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው በሙሉ ድምጽ ጸድቋል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ያቀረቧቸው ካቢኔዎች የለዩባቸውን ነጥቦች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ካቢኔዎችን ለመለየት ስለተጠቀሟቸው የግል ብቃት በዝርዝር ሲያስረዱ ሕዝቡ መንግሥትን ለማጽናትና ለማስቀጠል ምርጫ ላይ አደራውን ለመንግስት የተወ በመሆኑ አደራውን መሸከም የሚችሉ እንዲሆኑ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሕዝብ የጣለባቸውን አደራና ታላቅ ኃላፊነት የሚገነዘቡ፣ እንዲሁም ሕዝብ አጉልቶ የሚጠይቀውን ሙስና የሚጠየፉና ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ፣ ብሎም ሕዝብ አብዝቶ የሚጠይቀውን አገልግሎት ለመስጠት ማገልገል መታደልም ጸጋም ነው ብለው የሚያምኑ እንዲሆኑ ጭምር ጥረት መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እስከ 2050 የሚዘልቅ ታላቅ የመደመር ስትራቴጂ ማዘጋጀቷን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ታላቅ ስትራቴጂ በቅጡ የተረዱና በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ የተቀመጡ አበይት ነጥቦችን ከነዝርዝር እሳቤያቸው የተገነዘቡ ግለሰቦች ላይ ለማተኮር ተሞክሯል ብለዋል፡፡

የዜጎችን ጥቅም በተመለከተ ዕጩ ካቢኔዎችን ለመምረጥ የተሄደበትን መንገድ ሲያስረዱም፡-

“የኢትዮጵያ ዕድገት፣ ለውጥና መሻሻል እያንዳንዱን ዜጋ የማይነካ ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ መንገድ ስንሰራ ደሃው የሚራመድበትና ብስክሌት የሚያሽከረክርበት መንገድ መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎችን የሚነካ ዕድገት ለማድረግ በሂደት ብቻ የሚረኩ ሳይሆኑ በውጤት ደረጃ የሚያስቡ ግለሰቦች ተጽዕኖ የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል፡፡” ብለዋል፡፡

ከብቃትና ልምድ በተጓዳኝ ጾታን፣ እምነትንና ብሄርን ታሳቢ ካላደረግን አሁን ያለችውን ሕብረብሄራዊት ኢትዮጵያን ማጸባረቅ ስለማንችል ይህንንም በተቻለ መጠን ከግምት ያስገባ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል ሲሉም የካቢኔዎቹ ጾታ፣ እምነትና ብሄርን ታሳቢ ያደረገ ምርጫ ስለመደረጉ አረጋግጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ኢያሱ ታዴዎስ