ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር የደን ልማትና ጥበቃ ተግባር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ።
የዞኑ ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት መምሪያ የ2018 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ማጠቃለያ ጉባኤ እና የ2019 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በዚሁ መድረክ እንደገለጹት፤ የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር የደን ልማትና ጥበቃ ስራ በተቀናጀ መልኩ መከናወን አለበት።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በተለይም የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ያወሱት አቶ አበራ፤ በዞኑ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ስራ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን አመላክተዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት ከጉራጌ ልማት ባህል ማህበር ጋር በጋራ በመሆን ከ500 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለው በየአካባቢው እየለሙ እንደሆነና ተግባሩ አበረታች በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የደን መመናመን ችግርን ለመቅረፍ የደን ልማቱ ላይ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅም አቶ አበራ አስገንዝበዋል።
የጉራጌ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ እንዳለ ስጦታው በበኩላቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ ተግባር እያከናወነች ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ፤ በሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ሞዴል ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የምግብ ምርታማነትን በማሳደግና የደን ሽፋንን በማሳደግ ረገድ የጎላ ድርሻ አለው ብለዋል።
በዞኑ በ2011 ዓ.ም 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በተከናወነው የተቀናጀ የአረንጓዴ አሻራ ስራ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አቶ እንዳለ ገልጸዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ችግኞችን በመለገስ ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶችን በመንከባከብ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ አህጉራዊ የሰላም ድልድይ እየገነባች እንደሆነም አንስተዋል።
የጉራጌ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ የልማት ዕቅድ አስተባባሪ አቶ ታዱ ጋሚ የመወያያ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት የዞኑን የደን ልማት በማስፋፋት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለዘርፉ ባለሙያዎች ወቅቱን የጠበቀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ አንደሆነ ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም መድረኩ ለቀጣይ ስራቸው የሚያዘጋጅ እንደሆነ ገልፀው፤ ደን ለሰው ልጅ ህይወት አሰፈላጊ በመሆኑ በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።
የአካባቢ ጥበቃና ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን የተሾሙት አቶ መለሰ አለሙ የሥራ ርክክብ አደረጉ
ባህላዊ እሴቶችን የማልማት፣ የማበልፀግ እና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
ከ640 ሄክታር በላይ መሬት በካሳቫ መሸፈኑን በኮሬ ዞን የሳርማሌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ