በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን የተሾሙት አቶ መለሰ አለሙ የሥራ ርክክብ አደረጉ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን የተሾሙት አቶ መለሰ አለሙ የሥራ ርክክብ አደረጉ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ መለሰ አለሙ ዛሬ ከቀድሞው ኃላፊ ዶክተር መሐመድ ኑርዬ ጋር የሥራ ርክክብ አድርገዋል።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑርዬ፤ ተቋሙን በኃላፊነት በመሩባቸው ጊዜያት ከጎናቸው ለነበሩ የማኔጅመንት አባላትና ለመላው የቢሮው ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ያስታወሱት ኃላፊው፤ አዲሱ አመራር በቀጣይ ያልተሠሩ ሥራዎችን በቅንጅትና በመናበብ እንዲያከናውን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያለውን የመሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት የተሰጣቸውን ሕዝባዊ አደራ በታማኝነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በመሠረተ ልማት ዘርፍ በክልሉ የተጀመሩ ሥራዎችንም በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የሠራተኛውንና የአመራሩን አቅምና ተነሳሽነት በማቀናጀት እንዲሁም በመደመር እሳቤ ተቋሙን ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩ ያብራሩት ኃላፊው፤ ይህንንም ግብ ለማሳካት ከተቋሙ ሠራተኞችና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቢሮው የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት፤ ክልሉ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ለተሠሩት የመሠረተ ልማት ሥራዎችና ለቀድሞው ኃላፊ የአመራር ጥበብ ምስጋና አቅርበው፤ ከተቋሙ አዲስ ኃላፊ ጋር በመሆን የተጀመሩ ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቢሮው ምክትል ኃላፊዎች እና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን