ባህላዊ እሴቶችን የማልማት፣ የማበልፀግ እና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
ባህላዊ እሴቶችን የማልማት፣ የማበልፀግ እና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በዙሪያ ወረዳው የጋንታ ደሬ የመስቀል በዓል “ሶፌ” ስነ-ስርዓት በሾሽኔ ገበያ በድምቀት ተከብሯል።
በጋሞ ዞን ከሚገኙ 42 የጋሞ ደሬዎች አንዱ የሆነው የጋንታ ደሬ የመስቀል “ሶፌ” ስነ-ስርዓት በጋንታ ካንቻማ ኦቾሌ ቀበሌ ሾሽኔ ዱቡሻ ባህላዊ ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ በደማቅ ሁኔታ ሲከበር የበዓሉን መጀመር የጋንታ ባላባት ካቲ ፆና አባ በምርቃት አብስረዋል።
የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ባህል ስፖርትና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሶፎኒያስ ቲቲዮስ ፤ የዮ… ማሳቃላ በዓል ከአቀባበል ምዕራፍ እስከ ሽኝት ድረስ በልዩ ኩነቶች ታጅቦ እንደሚከበር ገልፀው፤ ይህንን ቱባ ባህል የመጠበቅና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የዮ… ማስቃላ በዓል በበርካታ ማህበራዊ ክዋኔዎች ታጀቦ መከበሩን እና የሽኝት ስርዓት ላይ መድረሱን አውስተው፤ ይህን እሴት የቱሪስት መስህብ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የጋሞ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማዜ ሸቀኔ በበኩላቸው፤ ዮ… ማስቃላን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ባህላዊ እሴቶችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ኩነቱ የህዝቦችን አንድነት እና አብሮነት ከማሳደግ የተሻገረ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።
የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ታደሰ፤ እንደ “ሶፌ” ያሉ ማህበራዊ መስተጋብሮችን በይበልጥ ለማጎልበት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከ “እንግጫ” ጀምሮ ሲከበር የቆየው በዓሉ ከጋሞ ደሬዎች መካከል አንዱ በሆነው የጋንታ ደሬ የሽኝቱ አካል የሆነው “ሶፌ” ስነ-ስርዓት መከናወኑን ገልፀዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ማጋ ምትኩ ምሻ ካራ እና አባገዳ ደምበላ በደቻ በሰጡት አስተያየት፤ ባህሉን ጠብቆ ከማቆየት ባሻገር አብሮነትን በማስቀደም በጋራ ማክበራቸውን እና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በበዓሉ ከአጎራባች ክልል ኦሮሚያ የመጡ የጉጂ አካባቢ ነዋሪዎች፣ የዘይሴ ብሔረሰብ አባላት፣ የአከባቢው ተወላጆች፣ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች እና የመንግሥትና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር የደን ልማትና ጥበቃ ተግባር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን የተሾሙት አቶ መለሰ አለሙ የሥራ ርክክብ አደረጉ
ከ640 ሄክታር በላይ መሬት በካሳቫ መሸፈኑን በኮሬ ዞን የሳርማሌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ