የሜሲ ታሪካዊ የስንብት ምሽት በቦነስ አይረስ
አርጀንቲና ለዓለም ካበረከተቻቸው ታላላቅ ስጦታዎች አንዱ የሆነው ሊዮኔል ሜሲ፣ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚያደርገውን የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ሌሊት 8 ሰዓት ላይ በኢስታዲዮ ሞኑሜንታል ከቤኒን ጋር በሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ አጠናቆ በክብር ይሰናበታል።
ይህ ታላቅ ስንብት የዓለምን ትኩረት የሳበ ቢሆንም፣ የሜሲ እና የአርጀንቲና ሕዝብ የፍቅር ጉዞ ግን ከመነሻው አንስቶ እስከመድረሻው ድረስ አልጋ ባልጋ አልነበረም።
ሜሲ በዓለም አቀፍ መድረክ መድመቅ ከጀመረበት ዕድሜው ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ቢወደድም፣ በአገሩ አርጀንቲና ግን ለዓመታት ከፍተኛ ውግዘት፣ ተቃውሞ እና አልፎ ተርፎም ውርጅብኝ ገጥሞት ነበር።
አርጀንቲናዎች ታላቁን ዲያጎ ማራዶና በሚያስደንቅ አኳኋን ይወዱ ነበር።
ማራዶና ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ሃይማኖት እና ስለ ማህበራዊ ጉዳዮች ግልጽ አቋም ያለው፣ ስሜቱን በግልጽ የሚያሳይ ነበር። ሜሲ ግን ዝምተኛ፣ ቁጥብ እና በአደባባይ መድረኮች ፖለቲካዊ አቋም ማራመድ የማይፈልግ በመሆኑ ብዙዎች “አርጀንቲናዊ አይደለም” እስከ ማለት ደርሰዋል።
የማራዶና አጨዋወት በሃይል፣ በደም እና በታጋይነት የተሞላ ሲሆን፣ የሜሲ ጨዋታ ግን እጅግ ፍጹም እና ቀላል የሚመስል በመሆኑ “ለአርጀንቲናዊ ጣዕም ቀዝቃዛ ነው” በሚል ይተች ነበር።
የሜሲ እና የአርጀንቲና ሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረው እ.ኤ.አ በ2011 የኮፓ አሜሪካ ውድድር ላይ አርጀንቲና ባዘጋጀችው ውድድር ስትሰናበት በደረሰበት የፉጨት እና የነቀፌታ ማዕበል ነበር። ይሁን እንጂ የሜሲ ጽናትና ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁሉንም አሳመነ።
ነገሮች መለወጥ የጀመሩት ከ2021 የኮፓ አሜሪካ ድል ጀምሮ ነው። በመቀጠልም በ2022 የካታር የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ድል እና ሌሎች ተከታታይ ስኬቶች አርጀንቲናውያን ለሜሲ ያላቸውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ቀይረውታል።
ከሀገሪቱ ሕዝብ ከ10 በመቶ በላይ (5-6 ሚሊዮን ሕዝብ) በቦነስ አይረስ ጎዳናዎች ወጥቶ ፍቅሩን አሳይቷል።
ባለፉት ወራት ውስጥ ግን በሜሲ ሕይወት ውስጥ ትላልቅ ውጣ ውረዶች አልፈዋል። ወላጅ አባቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት፣ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውጤት ጥሩ ያልነበሩለት ቢሆንም ሜሲን ከሕዝቡ ጋር ይበልጥ አቀራርበውታል።
አርጀንቲናውያን በቴሌቪዥን ማያ ገጾች ላይ የሜሲን የሀዘን ጊዜያት ሲከታተሉ፣ “ከእንግዲህ በጭራሽ ጀርባ አንሰጠውም” የሚለውን ውሳኔ በልባቸው አጽድቀዋል።
ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከት፣ አርጀንቲና ለሜሲ የነበራትን አመለካከት በመለወጥ ታሪካዊ ስህተቷን አርማለች።
አሁን ላይ ለብዙ ዘመናት ሲደርሱበት የነበሩት ትችቶችና ጥርጣሬዎች ወደ ፍጹም አድናቆትና ውዳሴ ተቀይረዋል።
ዛሬ ማታ በቦነስ አይረስ በሚደረገው ስንብቱ ላይ ሜሲ የሀገሩ ታላቅ ምልክት ሆኖ ይሸኛል፤ ይህ ታሪክም በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ለዘላለም የሚታወስ ድንቅ ታሪክ ሆኖ ይኖራል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ከ29 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙት ኢትዮጵያ እና ሴኔጋል
ሳዲዮ ማኔ በትውልድ መንደሩ ባምባሊ 20 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ጀመረ
ካይ ሃቨርትዝ ጉዳት አጋጠመው