በክረምት የታየው የበጎ ተግባር ተሳትፎ በበጋ ወራትም በማስቀጠል ደጋፊ የሚሹ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

በክረምት የታየው የበጎ ተግባር ተሳትፎ በበጋ ወራትም በማስቀጠል ደጋፊ የሚሹ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

በባስኬቶ ዞን የክረምት በጎ ተግባራት ማጠቃለያና የ2019 ዓ.ም የበጋ በጎ ሥራ ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የዞኑ ወጣቶች ጉዳይና የበጎ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ጉጆ እንዳሉት፤ በክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ18 መስኮች የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

አገልግሎቱን ከዞን ባሻገር ወሰንና ድንበር ተሻጋሪ በማድረግ ከተለያዩ አጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር የእርስ በርስ ትስስርን ለማጠናከር ማገዙን አመላክተዋል።

በተካሄዱ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ከህዝብና መንግስት ሊወጣ የነበረ ከ300 ሚሊየን በላይ ብር ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

የባስኬቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር በዛብህ ገበዬሁ በመድረኩ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ ባሳለፍነው ክረምት ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በቤት እድሳትና ግንባታ፣ በማጠናከሪያ ትምህርትና ስልጠና፣ በጤና አገልግሎት፣ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት፣ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ፣ በሠላም ግንባታ ሥራዎች በስፋት በመሳተፍ የሚበረታታ ውጤት አስመዝግበዋል።

ዋና አስተዳዳሪው በበጎ አገልግሎት መርሃ ግብር ለተሳተፉ ወጣቶች፣ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት፣ አመራሮች እና የማህበረሰብ አባላት ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ በ2018 ዓ.ም በክረምት ወራት የተከናወኑ ዝርዝር በጎ ተግባራት እና የ2019 ዓ.ም የበጋ በጎ ሥራ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባር ለአቅመ ደካሞችና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቤት መስራት፣ በአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ አሻራ በርካታ ችግኞ የተተከሉ ሲሆን የጽዳትና የውበት ሥራዎች መከናወናቸው በሪፖርት ተመላክቷል።

በጤናና ግብርና መስክ፣ በትራፊክ አደጋ ቅነሳ፣ የምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ በ18ቱ መስኮች የተከናወኑ ተግባራት ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

በዞኑ በግልና በቡድን በመሆን በበጎ ተግባር ላይ ሲሳተፉ የቆዩ አስተያየት ሰጪዎች እንደተናገሩት፤ በክረምት ወራት አቅመ ደካማ ወገኖችን እና የመማር አቅም የሌላቸውን ወገኖች ሲደግፉ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በበጋው ወራትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በጎነት የህሊና እርካታን የሚፈጥርና በፈጣሪ ዘንድም ዋጋ ያለው ተግባር በመሆኑ ሁሉም ማህበረሰብ እንዲሳተፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክንፉ ሻቦ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ፤ በጎነት የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ፖሊሲ ማሳያ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይ በጋ ወራትም በክረምቱ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ከተሞክሮዎች በመማር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን