የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ውብና ጽዱ አካባቢ ለመፍጠር የደን ልማትና ጥበቃን ማጠናከር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ ገለጸ

 መምሪያው የ2018 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ማጠቃለያ ጉባኤ እና የ2019 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ አመት እቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ነው።

የጉራጌ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ እንዳለ ስጦታው በመድረኩ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት፤ የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ አካባቢ በመፍጠር የደን ልማትና ጥበቃ ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚና ጽዱ አካባቢ ለመገንባት እንደ ሀገር የተጀመሩትን ኢኒሼቲቮች በዞኑ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየተከናወነ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በበጀት አመት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን በማንሳት በቀጣይ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድሙ አበራ፣ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ኸይሩ መሀመድ፣ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጠጄ ደነቀ እና የዞኑ የማኔጅመንት አባላት፣ የሁሉም ወረዳ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በመድረኩ እየተሳተፉ ይገኛል።

ዘጋቢ ፡- ደጋጋ ሂሳቦ ከወልቂጤ ጣቢያችን