የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የሚጫወቱትን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የሚጫወቱትን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 24/2019 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የሚጫወቱትን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው የቤንች ሸኮ ዞን ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኮጁ ባዲካች ተናገሩ።

የአማን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ለ22ኛ ዙር በተለያዩ መስኮች በደረጃ አራት ያሰለጠናቸውን 250 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡

የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ሁለት ዋና ዋና አላማዎችን ይዘው እየሰሩ ሲሆን እነዚህም የክህሎት መር ስልጠና እና የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ናቸው።

በዚህም የአካባቢውን የገበያ ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ የአጭር እና ረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና በማሻሻል ለኢንተርፕራይዞች ማሻገር አላማ አድርጎ እየተሰራ መሆኑን የአማን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን አለማየሁ ተናግረዋል።

ኮሌጁ ባሳለፋቸው 25 ዓመታት ውስጥ በተግባር እና በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የሰለጠኑ 21 ሺ 559 ሰልጣኞችን አሰልጥኖ ለፍሬ ማብቃቱንም ጠቁመዋል።

ዘንድሮም ለ22ኛ ዙር በአስር የተለያዩ የስልጠና ዘርፎችም 250 ሰልጣኞችን በደረጃ አራት ማስመረቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ኮሌጁ ከመደበኛ ስልጠናው ባለፈ በአጫጭር ስልጠና ዘርፍም ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ 2 ሺ174 ሰልጣኞችን አሰልጥኖ ማስመረቅ እንደቻለ ነው አቶ መስፍን የጠቆሙት።

በምረቃው ስነ-ስርአት ላይ የተገኙት የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ለዊ በበኩላቸው፤ የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ሰውን ለስራ ብቻ የሚያበቁ ብቻ ሳይሆኑ የሀገርን ምርት እና ምርታማነት የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በሰለጠኑበት ሙያ ለሀገራቸው እድገት እና ለውጥ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በከተማው እየታየ ያለውን ፈጣን እድገት አንዲያስቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኮጁ ባዲካች በበኩላቸው እንዳሉት፤ የዛሬው ምረቃታችሁ የህይወታችሁ ጉዞ ጅማሬ ነው።

የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ የተግባር ሙያ ማስጨበጫ ተቋመት በመሆናቸው ተመራቂ ተማሪዎች በጨበጡት እውቀት እና ክህሎት ስራ ጠባቂዎች ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪ በመሆን እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ሊለውጡ ይገባል ብለዋል።

በኮሌጁ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ተመስገን ሽብሩ እና ተማሪ የሺ አምበር በሰጡት አስተያየት፤ በኮሌጁ በቀሰሙት የሙያ ዘርፍ ስራ ፈጣሪ በመሆን ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን